ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በማይገኙ የትግራይ ሕዝብ የወከላቸው የምክር ቤቱ አባላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ባለፉት ሁለት የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ከአንድ ተወካይ በስተቀር ከትግራይ ክልል የተወከሉ የምክር ቤት አባላት አለመገኘታቸውን ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ በኩል ተወካዮቹ እንዲገኙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የተናገሩት አፈ ጉባዔው፤ አባላቱ ባለመገኘታቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ግን አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ አሳስበዋል።
ማንኛውንም ችግር በውይይት፣ በህግና አሠራር መፍታት እንጂ ሀገርን የማፍረስና ህግን የመተላለፍ ተግባር መፈፀም የለበትም ያሉት አፈ ጉባዔው፤ ዘንድሮ የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከ90 በመቶ በላይ የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦቱን ማጠናቀቁን አረጋግጠናል ብለዋል።
በምርጫ ሂደቱ ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የውድድር ሜዳ እንዲፈጠር መሠራት አለበት በማለት የተናገሩት አፈ ጉባዔው፤ ምርጫው ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከለውጡ ጋር የተለያዩ ማሻሻያዎች በማድረግ ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት እየሠራ ይገኛል ተብሏል። ምክር ቤቱ ወደ ሕዝቡ ይበልጥ በመቅረብ እየሠራ ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፣ በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በገንዘብና ቁሳቁስ 40 ሚሊየን ብር እንደለገሰ ገልፀዋል።