ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ጥቅምት 8 እና 11 (በተለይም ትናንት) በሁለት ቀበሌዎች በተፈፀመ ጥቃት የ31 ሰዎች ህይወት ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ይህን ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ 16 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።
እነዚህ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል አንድ የፖሊስ አባልና አራት አመራሮች እንደሚገኙበት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን ይፋ አድርገዋል።
በወረዳው ጥቅምት 8 እና ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም በሁለት ቀበሌዎች በተፈፀመ ጥቃት የ31 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና አምስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ 1 ሺኅ 480 አባወራዎች ደግሞ ተፈናቅለው በቢፍቱ ከተማ እንደተጠለሉና ጊዜያዊ እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።