ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዮ ሥፍራዎች በተቀሰቀሰ ኹከት ለወደሙ ኢንቨስትመንቶች ካሳ እንደማይከፍል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ገለጸ።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በዚህ ኹከተና ገርግር በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች 89 የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል መውደማቸውን ግን በይፋ አረጋግጧል።
ከሦስት ወራት በፊት በክልሉ በተስተዋለው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ከተሞች መካከል ሻሸመኔ ፤ ዝዋይ የሚገኙበት ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መድረሱ አይዘነጋም።
የሃጫሉን ግድያን ተከትሎ በኢንቨስትመንት ድርጅቶች ላይ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲሰላ ከ3 ቢሊዮን በር በላይ እንደሚሆን ለቢቢሲ የጠቆሙት የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዋሲሁን ጎልጋ፤ ኮሚሽኑ ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ የተለያዩ ድርጅቶችን ለማገዝ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ መቆየቱንም ገልጸዋል።
“የደረሰው ጉዳት ከተለየ በኋላ ከፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመወያየት ከዚህ በፊት መኪና እና ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ያስገቡ አሁንም በድጋሚ በነፃ እንዲያስገቡ፣ የባንክ ብድር ያለባቸው ደግሞ የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጣቸው ተወስኗል” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ጉዳት የደረሰባቸው እነዚህ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ከዚህ በፊት የመሬት ጥያቄ አቅርበው ከነበረ በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ ውሳኔ መተላለፉን አስረድተዋል።
በመሆኑም ድርጅቶቹ ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ከማገዝ ውጪ ለደረሰው ጉዳት መንግሥት የሚከፍለው ምንም ዓይነት ካሳ እንደሌለና እንዲሁም ለመክፈል ቃል የሚገባው ነገር አለመኖሩንም ም/ኮሚሽነር ዋሲሁን ጎልጎ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ በነበሩት ኹከትና ጥቃቶች ጉዳት ከደረሰባቸው 89 ድርጅቶች መካከል ጥቂቶቹ ወደ ሥራ እየተመለሱ ናቸው ያሉት ሓላፊው፤ በተደጋጋሚ በኦሮሚያ ክልል በሚፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳ፣ በኢንቨስትመንት ድርጅቶች ላይ በሚደርሰው ጉዳት ሥራ ላይ ያሉ ኢንቨስትመንቶች በሙሉ አቅማቸው እንዳይሠሩ ጫና እያሳደረባቸው እንደሚገኝም አልሸሸጉም።