ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሠፊው የአማራ ሕዝብ ለዓመታት ለፍትህ፣ ለነፃነት እና ለአብሮነት ሲታገል ቢኖርም እስካሁን በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ ፍትህና የህግ የበላይነት ሰፍኖ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በሰላም ፣ በነፃነት እና በደስታ መኖር የሚቻልባት አገር ባለቤት መሆን አልተቻለም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አሰታወቁ።
ችግሮች ከመቀነስ ይልቁቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግፍና መከራው እየተጠናከረ የአማራ ሕዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፉና በገፍ መፈናቀሉ ተስፋፍቶ ቀጥሏል ያሉት የለውጡ ቡድን አጋፋሪ፤ ይህንን ሁኔታ ለመረዳት ብዙም ሩቅ ሳንሄድ ይህንን አንድ አመት ብቻ ወስዶ የተፈጸመውን ጥቃት መገምገሙ ብቻ በቂ ነው በማለት የችግሩን ጥልቀት አሳይተዋል።
“ከጥቅምት እስከ ጥቅምት ያለው አንድ አመት ብቻ በግልፅ የሚነግረን ግፍና መከራው ተጠክሮ መቀጠሉን ነው። ማለቂያ የሌለው የጅምላ ጭፍጨፋ፣በገፍ መፈናቀል፣ የዘመናት የልፋት ውጤት የሆነ ንብረት ውድመት በየሳምንቱ መርዶ መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል” ያሉት የአማራ ክልል ተወላጁ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ በመሆኑም ነገሩን ላለማባባስ ሲባል በዝምታ ማለፋ የሚጎዳ መሆኑን በተግባር እያየነው ነው ሲሉ ምሬት የተሞላበት ሀሳባቸውን በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ አስነብበዋል።
“በመሆኑ ያገባናል ባዮች በሙሉ ልንነጋገርበት ይገባል። ይህ በአማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈፀመ ያለው በማንም ሕዝብ ሳይሆን በጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች ሴራ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጋርነት የሚያሰልፍ የትግል አቅጣጫ ነድፎና ስትራቴጅያዊ ግብ ወስኖ በጋራ መንቀሳቀስ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም” በማለት ከለውጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪነታቸውን ያሳዮበትን ንግግር ያደረጉት የውጭ ሚኒስትሩ፤ በክስተት ላይ ያነጣጠረ ጩኸት አልቃሻ ከማድረግ የዘለለ ጥቅም እንደሌለ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።