ትናንትናና ዛሬ ስለቋንቋ ትምህርት ሁለት አዲስ ዜና ሰማሁ፤ አንደኛው በቻይና ሀገር የአማርኛ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀግብር ደረጃ ማስተማር መጀመሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው በትግራይ ክልል የግእዝ ቋንቋ በትምህርት አይነትነት ለመስጠት መወሰኑ ነው፡፡
የቻይናው ስነልሳናዊ እውቀትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ አማርኛ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የአፍ ማፍቻና የሁለተኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉት፣ ከአረብኛ ቀጥሎ በርካታ ተናጋሪዎች ያሉት የሴም ቋንቋ ነው፡፡ አማርኛ በቋንቋ ትምህርት ደረጃ ከሚያስተምሩ ሀገሮች መካከል ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ . . የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡ ቻይናም በዲግሪ ደረጃ አሁን ይጀመር እንጂ፣ ቀደም ብሎም በቋንቋ ትምህርትነት ይሰጥ ነበር፡፡ አማርኛ ከመቶ ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር የስራ ቋንቋ በመሆኑ ቻይናዎቹም ሆኑ፣ ሌሎች ለዜጎቻቸው የስራ እድል ይፈጥሩበታል፡፡ በተለይ ዛሬ በተንሰራፋብን የብሄር ፖለቲካ የተነሳ አማርኛን አናስተምርም የሚሉ ክልሎች እየሰማን ስለሆነ፣ ይህ ካልተለወጠ ነገ ብሄር የለሌው አማርኛ ተናጋሪ ባለሙያ ከቻይና ልናስገባ እንችላለን፡፡
የቻይና ውሳኔ አማርኛ ‹‹በዚህ ደረጃ- በዚያ ደረጃ›› ብቻ ነው የምናስተምረው የሚሉ ክልሎች የቻይና ውሳኔ ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸው ዘንድ እመኛለሁ፡፡ የቋንቋ እውቀት የስራ እድልን ያሰፋል፤ ተግባቦትን ያሳልጣል፡፡ በምንም መንገድ አይጎዳም፡፡ ለዚህ ነው ‹‹ጠርዝ ላይ›› በሚለው መጽሀፌ በሚቀጥሉት አስርና አስራአምስት አመታት የስራ ቋንቋዎቻችን አምስት እንዲደርሱ ሀሳብ ያቀረብኩት፡፡ ይህም በአዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ ውስጥ (በፖሊሲ ደረጃም ቢሆን) ተግባራዊ ስለተደረገና ሰሚ ስላገኘሁ ደስ ብሎኛል፡፡
አማርኛ የሚናገሩ ፖለቲከኞቻችን አማርኛን ልጆቻቸው እንዳይማሩ መከልከል ተገቢ እንዳልሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ በርካታ ቋንቋዎችን ቢማር አእምሮው ይዳብራል፤ የስራ እድሉ ይሰፋል፡፡ ጉዳት የለውም፡፡
የትግራይ ክልል ውሳኔ ቅን ሀሳብ ነው፤ የስነልሳን እውቀትን ግን ጠለቅ ብሎ አላየም፡፡ ግእዝ የሞተ ቋንቋ ነው፡፡ አንድ ቋንቋ ሞተ የሚባለው በቋንቋው አፉን የሚፈታ፣ ለእለት ተእለት ኑሮው የሚጠቀምበት፣ ‹‹የእኔ ቋንቋ ነው›› የሚለው ማህበረሰብ ሲያጣ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ግእዝ ሞቷል፡፡ እንደግእዝ ያሉ በርካታ የጽህፈት ቅርስ ያላቸው ቋንቋዎች ቢሞቱም በትምህርትነት ይሰጣሉ፡፡ ይህ ግን ቋንቋውን ለተለያየ ጉዳይ ለሚፈልጉ ሰዎች ነው፤ ይህ በአብዛኛው በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጥ ነው፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ግእዝን ማስተማር ታላቅ ብክነት ነው፡፡ ስንቱ ነው በቋንቋው ምርምር የሚሰራው? ይግባቡበታል እንዳይባል ተናጋሪ ማህበረሰብ የለውም፡፡
የዚህ ውሳኔ ሌላው ችግር በትምህርት አይነትነት የሚሰጡ ቋንቋዎች ብዛት ነው፡፡ ባደረኩት ንባብ በትምህርት ቤት ከሶስት በላይ የቋንቋዎችን የሚያስተምሩ ሀገሮች አላጋጠሙኝም፡፡ እኛም ሀገር እንዲሁ ነው፤ ተማሪዎች የራሳቸውን ቋንቋ፣ አንድ የሀገሪቱን ኦፊሻል የስራ ቋንቋ (ከአምስቱ መርጠው) እና እንግዚዘኛን ይማራሉ፡፡ እያንዳንዳቸው በሳምንት ሶስት ክፍለ ጊዜ ቢሰጣቸው እንኳን፣ በሳምንት ካሉት ክፍለ ጊዜዎች ዘጠኙን ቋንቋ ይይዛል፤ አንድ ብንጨምር ቋንቋ 12 ክፍል ጊዜ ባሳምንት ሊሆን ነው፡፡ በሳምንት ካሉት 30 ክፍለጊዜዎች 12ቱን ቋንቋ ከያዘ፣ የሌሎቹ ይይዘት ትምህርቶች ጊዜ ይጠባል፡፡ በመሆኑም የትግራይ ክልል ግእዝ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ቢያስተምርና የሚፈልጉ እንዲማሩት ቢያደርግ የተሸለ ጥቅም አለው፡፡