ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር በ115 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል ተባለ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደገለፀው ከሆነ በ16 በመቶ ገቢ መጨመሩን እና በአጠቃላይ 838 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ይፋ አድርጓል።
ሚኒስቴሩ የበጀቱ የሩብ ዓመት አፈጻጸም የማዕድን ዘርፍ የእቅዱን 300 በመቶ እና 205 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲያሳካ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ 95 በመቶ እና 94 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል።
የግብርና ውጤቶች የዕቅዱን 73 በመቶ እና 541 የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማስገኘታቸውን የጠቆመው መረጃ፤
ለወጪ ንግድ መሻሻል ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው የወጪ ምርቶች ውል ምዝገባና አፈጻጸም መመሪያ መሆኑም እንደሆነም አስረድቷል።
በወጪ ምርቶች ንግድ ላይ የሚፈጸሙ ውሎችን ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው የውል ምዝገባ አፈፃፀም ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ ምርት ያላግባብ በክምችት እንዳይያዝ፣ የወጪ ምርቶች ግብይት ዓለም ዐቀፍ ገበያ ጋር ተነባቢ እንዲሆን መደረጉ፣ እንዲሁም በወጪ ምርቶች ላይ የዋጋ መሻሻል ማስገኘቱ ለስኬቱ እንደአብነት ሚጠቀሱ ነጥቦች ናቸው ተብሏል።
በአንጻሩ የወጪ ንግድ የተሻለ እንዳይሆን እንደ ክፍተት ከታዩት መካከል ደግሞ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ደካማ ቅንጅት እና ወጥነት የሌለው የግብይት ሕጎች ትግበራ ለከፍተኛ ህገ ወጥ ግብይት በር መክፈቱ፣ ከፍተኛ የምርት መጠን በአቅራቢዎች መያዙ፣ የዓለም ዐቀፍ የምርቶች ዋጋ መቀነስ፣ የመጀመሪያ የግብይት ማዕከላት በበቂ ሁኔታ አለመሟላት እና በድንበር አካባቢ ያለው ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር የላላ መሆን በዋናነት ይጠቀሳሉ ሲል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መ/ቤቱ አስታውቋል።