ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚመጣ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ኃይልን ለመመከት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።
የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ፤ ሠራዊቱ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ ሀገርንና ሕዝብን የመጠበቅ ህገ መንግሥታዊ ሥልጣኑን የሚያስቆመው አካል እንደሌለ ነው የተናገሩት።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ነው ይህን ያሉት።
ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት ከሥነ ምግባር ጀምሮ የቴክኒክ፣ የትጥቅ፣ የአቅምና ሌሎች አጋዥ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሚገባ መጠቀም የሚችል፣ በማንኛውም ስፍራ ፈጥኖ ደርሶ ተልዕኮውን መወጣትና ማንኛውንም ጠላት መመከት የሚችልበት ጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ነው ጀነራሉ የተናገሩት።
በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግድቡ ከመጀመሩም ሆነ ውሃ ከመሞላቱ በፊት የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ይሰነዘሩ እንደነበርና ሰራዊቱ ይህንን በመገንዘብ ምንጊዜም በተጠንቀቅ የቆመ ነው ብለዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ኃይል በልዩ ኮማንዶ፣ በባህር ጠላቂ ሀይል፣ በአየር ወለድና መሰል አደረጃጀቶች የተደራጀና ማንኛውም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መሰናክል ሳይወስነው ግዳጁን የሚወጣ እንደሆነ ያብራሩት ሜ/ጀነራል ሹማ አብደታ፤ በተጨማሪም ሠራዊቱ በተለይ አሁን ካላው የፖለቲካ ሁኔታም ይሁን የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ የሀገርን ሰላም፣ የሰው ህይወትና ንብረት ለመጠበቅ በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ተንቀሳቅሶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የፖለቲካ ጉዳይ የፖለቲከኞች ነው ያሉት ጀነራሉ ሠራዊቱ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ሥራውን ለመሥራት የሚያስቆመው አካል እንደሌለ የገለፁት የጦር ሓላፊው፤
“የመከላከያ ሠራዊት የአንድ ክልል ወይም የግለሰብ አይደለም፤ ዓላማው የአገር ህልውና እንዲቀጥል፣ ሕዝቦች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ማድረግ እስከሆነ ድረስ ሁሉም የኔ ነው ብሎ መደገፍና ከጎኑ መቆም አለበት” በማለት የተናገሩት የልዮ ጦር አዛዡ፤ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መከላከያ እንደማይገባ ጠቁመው፣ ከዚህ ያለፈ ችግር ሲኖር ግን መከላከያ ቁንጮና የመጨረሻው መፍትኄ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።