አብን የጠራው ሠልፍ እውቅና የሌለው በመሆኑ መንግሥት እርምጃ እወስዳለሁ አለ

አብን የጠራው ሠልፍ እውቅና የሌለው በመሆኑ መንግሥት እርምጃ እወስዳለሁ አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና ||  የአማራን ሕዝብ እወክላለሁ በሚለው አብን (አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ)  የፊታችን ረቡዕ (ለመውሊድ በዓል ዕለት) በክልሉ ከተሞች የጠራው ሠላማዊ ሠልፍ ዕውቅና እንደሌለው የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

የአማራ የክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጠራው ሠልፍ ክልሉ እንዲረጋጋ ለማይፈልጉ ኃይሎች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚመች ነው ሲሉ  ሠልፉ ወቅቱን ያልጠበቀ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአማራ ክልልንም ሆነ ህዝቡን መሠረት በማድረግ በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ግጭት በመፍጠር ሀገር ለማተራመስ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች አሉ ያሉት አመራሩ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ዘር ማጥፋት የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱ ተገቢ እንዳልሆነና የክልሉ መንግሥትም እንደማያውቀው ገልጸዋል።
ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፣ ጥቅምት 22 ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ ለማካሄድ በፌስ ቡክ ጥሪና ቅስቀሳ እያካሄደ ይገኛል።
“ጸረ ለውጥ ኃይሎች የብሔር፣ የሃይማኖት እና የኢኮኖሚ አጀንዳ በመፍጠር አማራ በደል እንዲደርስበት እና ዝቅ እንዲል መሥራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል” ሲሉ የጥቃቱን መኖር ያልካዱት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዮኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር፤ የጥፋት ቡድኖቹ ይህ ዓላማቸው በክልሉ ውስጥ አልሳካ ሲላቸው በቅርቡ በቤኒሻንጉል አሁን ደግሞ በጉራ ፈርዳ ወረዳ ሠላማዊ ዜጎችን በግፍ እየገደሉ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በአብን በኩል የተጠራው ሰልፍ እውቅና የለውም ያሉት አቶ ግዛቸው፤ “ችግሩ ሰልፍ በማድረግ ብቻ አይፈታም፤ ሰልፍ መፍትኄ ቢሆን የክልሉ መንግሥትም ገዢውን ፓርቲ በማስተባበር ሰልፍ በጠራ ነበር” በማለት የአደባባይ ተቃውሞ ፍሬ አልባ እንደሆነ አስረድተዋል።
ጸጉረ ልውጦች ሰልፉን በመጠቀም ግርግር ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑ ስለሚታወቅ መንግሥት ለተጠራው ሠልፍ እውቅና አልሰጠውም ያሉት ባለሥልጣኑ፤ “በግምት አይደለም የምንነጋገረው። በተጨባጭ እዚህ ከልል ላይ ሰልፍ ቢካሄድ አሁን ባለው ሁኔታ ግጭቶች ይከሰታሉ፤ የተዘጋጁ የሚፈነዱ ቦምቦች አሉ” ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ በተጠራው ሰልፍ ላይ እንዳይሳተፍ፤ አስተባባሪዎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው፤ ሰልፍ በሚወጡም ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ከመግለጻቸው ባሻገር፤ ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ሰዐት ድረስ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ እንዳልቀረበም አረጋግጠዋል።

LEAVE A REPLY