ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያካሂዱት ውይይት እንደሚጀምር የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ይፋ አደረጉ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኋላ በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ውይይት በነገው ዕለት እንደሚጀመር የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ድኅረ ገጽ ላይ አስነብበዋል።
በትብብር መንፈስ፣ በፈቃደኝነት እና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ ሀገራቱ ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና ያቀረቡት ፕሬዝዳንት ራፋሞሳ፤ በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ በሚደረገው የሦስትዮሽ ውይይት ሰላማዊ እና ትብብራዊ መፍትኄ ለመስጠት በሦስቱ ሀገራት መሪዎች ዘንድ ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና ተነሻሽነት መኖሩን ገልፀዋል።
ሦስቱ ሀገራት ቴክኒካዊ እና ህጋዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በቀሪ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል ተስፋ ከወዲሁ የተጣለባቸው ሲሆን፤ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚደረስ ስኬታማ ስምምነት ቀጠናዊ ውህደትን እንደሚያፋጥን ፣ ለአፍሪካም ሆነ ለቀጠናው ቀጣይነት ያለው ልማት እና ትብብር ወሳኝ እንደሆነም ተነግሮለታል።