ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ምክንያት ላለፉት ሠባት ወራት ተቋርጦ የነበረው የገጽ ለገጽ ትምህርት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀመረ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ እና የትምህርት ሚንስትር ዶ/ር ጌታሁን በምንሊክ አጠቃላይ መሰናዶ ት/ቤት በመገኘት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የገጽ ለገጽ ትምህርት መጀመሩን በይፋ አውጀዋል።
ትምህርት ቤቶቻችን በድጋሚ የመዘጋት አደጋ እንዳያጋጥማቸው ተማሪዎች ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል።
“እኔም አስተምራለሁ” የሚለውን መርሀ ግብር በመጀመር ተማሪዎችን የፊዚክስ ትምህርት ያስተማሩት ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ሌሎች የማኅበረሰቡ ክፍሎች የመርሀ ግብሩን ዓላማ በመደገፍ ተማሪዎችን በማስተማር የዜግነት ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
በገጽ ለገጽ ትምህርት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተማሪዎች የንጽሕና መጠቀሚያ ቁሳቁስ ተበርክቷል፤ የእጅ መታጠብ ተግባር የተከናወነ ሲሆን፣ የተማሪዎች የመማሪያ ክፍሎች ጽዳትና አያያዝም ተጎብኝቷል።