በኤርትራ ብቸኛው ሜሎቲ ቢራ በኩፖን (መሸመቻ ካርድ) በሱቆች ብቻ እንዲሸጥ ተወሰነ

በኤርትራ ብቸኛው ሜሎቲ ቢራ በኩፖን (መሸመቻ ካርድ) በሱቆች ብቻ እንዲሸጥ ተወሰነ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎችና መጠጥ ቤቶቿን የዘጋችው ኤርትራ ቢራ በኩፖን መሸጥ ጀመረች።

በአስመራ ከተማ የሚገኘውና በኤርትራ ብቸኛው የቢራ ጠማቂ ፋብሪካ የምርት ውጤት የሆነው ሜሎቲ ቢራ በሱቆች በመሸመቻ ካርድ ወይም ኩፖን አማካኝነት እየተሸጠ ይገኛል።
ትግርኛ ተናጋሪ ታማኝ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ የዘገበው ቢቢሲ፤ ደንበኞች ቢራውን ማግኘት የሚችሉት በሱቆች ብቻ እንደሆነና አንድ ቢራ በዐሥር ናቅፋ (በ25 ብር በሚጠጋ) ዋጋ እየተሸጠ ነው ብሏል።
ኩፖኑን የያዙ ሰዎች በአንድ ሳምንት መግዛት የሚፈቀድላቸው የቢራ ብዛት ስምንት ጠርሙስ ብቻ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኤርትራ ዳቦ፣ ዘይት፣ ስኳርና ማሽላ የመሳሰሉትን መሰረታዊ ሸቀጦች በስርጭት በመሸመቻ ካርድ በቤተሰብ ቁጥር ልክ በቀበሌዎች ብቻ የሚሸጥ ሲሆን፤ ኤርትራውያን በተለይ ዳቦ ለመግዛት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዳቦ ቤቶች ተመዝግበው በየዕለቱ ጧት የቤተሰባቸውን ቁጥር መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲገዙ ተፈቅዶላቸዋል።
ሜሎቲ ቢራ እንደ ዳቦና ስኳር በሱቆች በመሸመቻ ካርድ መሸጡ አንዳንድ የመጠጥ ቤት ባለቤቶችን ቅር አሰኝቷል ነው የተባለው።በአስመራ የሚገኝና ስሙን ያልገለጸ  አንድ የመጠጥ ቤት ባለቤት  “የንግድ ፍቃድ ያለን ሰዎች ንግድ ቤታችሁን ዝጉ ፤ ለሠራተኞች ደሞዝ ክፈሉ ተብለን ስናበቃ እኛ ልንሸጠው የሚገባ ቢራ በሱቆች እየተሸጠ ይገኛል” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

LEAVE A REPLY