አብን አመራሮቹ በቢሮአቸው በታጣቂዎች መከበባቸውን ተከትሎ የጠራውን ሠልፍ መሰረዙን ይፋ አደረገ

አብን አመራሮቹ በቢሮአቸው በታጣቂዎች መከበባቸውን ተከትሎ የጠራውን ሠልፍ መሰረዙን ይፋ አደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ነገና እሁድ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች እና በአዲስ አበባ የጠራውን ሰልፍ መሰረዙን ገለፀ።

በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ዘር ማጥፋት የሚያወግዝ  የተቃውሞ ሰልፍ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፣ ጥቅምት 22 ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ ለማካሄድ ጥሪ አስተላልፎ እንደነበረ አይዘነጋም።
 “የተጠራውን ሰልፍ መምራት ስለማንችል ሰልፉ ተሰርዟል” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት የአብን የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ፤ ዛሬ ጠዋት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስለ ሠልፉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ምክክር እያደረገ ሳለ በፖሊስ እንደተከበበ፣ የፓርቲው አባላትም ከቢሯቸው መውጣትም ሆነ መግባት አለመቻላቸውን ይፋ አድርገዋል።
እንቅስቃሴያችንን ለመገደብ ሙከራ ተደርጓል፤ በዚህ ሁኔታ ሰልፉን መምራት ስለማንችል እንዲቀር ተወስኗል ያሉት አቶ ጣሂር፤ “ዛሬ ጠዋት ስብሰባ እያደረግን ነበር። ከሰዐትም ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ጥሪ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ቢሯችን በፖሊስ ተከብቧል። መግባትም ሆነ መውጣት አልቻልንም፤ ጋዜጠኞችም ወደ ቢሯችን መግባት አልቻሉም” ሲሉ ተናግረዋል።
ቢሯቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት መከበቡን የጠቆሙት  የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው፤ “ከ5፡30 ጀምሮ ቢሮአችን ተከብቧል። ጭምብል በለበሱ እና በኃይል በታጠቁ ፖሊሶች ነው የተከበብነው። እዚህ ደረጃ የሚያደርስ ነገር እንደሌለ ለፖሊስ አባላቱ ነግረናቸዋል። እነርሱ ግን ታዘን ነው ስለአሉ ምንም ማድረግ አልቻልንም” በማለት አብን የጠራውን ሠልፍ ለመሰረዝ የተገደደበትን ምክንያት ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY