ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአፋር ክልል ገዳማይቱ ተብላ በምትጠራው አካባቢ ትንንት ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ፤ በትምህርት ቤት ውስጥ የተገደሉት የትምህርት ሚኒስቴር ሁለት ሠራተኞች መንግሥት “አሸባሪ” ባላቸው ኃይሎች እንደተገደሉ ተገለፀ።
የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ሓላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመቆጣጠር የተሠማሩት የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኞች የነበሩት አቶ ሙላት ፀጋዩ እና አቶ አበባው አያልነህን ጨምሮ በክልሉ በደረሰ ጥቃት ዐሥር ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
በአፋር ክልል ዞን ሦስት ገለአሎ በተሰኘች ወረዳ፣ ሰርከሞና ቴሌ ቀበሌ በሚባል መንደር የሚገኙ የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ ላይ ጥቅምት 16፣ 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዐት በተፈፀመ ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውም ይፋ ተደርጓል።
የሽብር ጥቃት ነው የተባለው ግድያ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ያነጣጠረ ነው ያሉት ሓላፊው፤ የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኞቹ በጥይት መገደልም ከዚህ የሽብር ጥቃት ጋርም የተያያዘ ነው ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያትም በስፍራው የተለያዩ ግጭቶች እንደሚያጋጥሙ ያስታወሱት አቶ አህመድ እንዲህ አይነቱ የሽብር ጥቃት ሲያጋጥም ግን ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን እንደሆነም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በአፋምቦ ወረዳ፣ ኦግኖ ቀበሌ በተመሳሳይ መልኩ ሌሊት ላይ ሴቶችና ሕጻናት ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ተፈፅሞ ቁጥራቸውን ያልገለጹት ሰዎች መገደላቸውን ም አመራሩ አስታውሰዋል።
ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ የኢትዮ-ጂቡቲ አውራ ጎዳናና ዓለም ዐቀፍ መተላለፊያ ድንበር ሲሆን፣ ጥቃቱን ያደረሱት አካላት በህገ ወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ተሰማርተው የነበሩና ያ እንቅስቃሴያቸው የተገታባቸው ኃይሎች፣ በአካባቢው የሚኖሩ የሶማሌ ኢሳ ጎሳ ማኅበረሰቦችን ከለላ በማድረግ ህዝቡን እንዳጠቁ ነው የተነገረው።
አሸባሪ ለየትኛውም አይወግንም እነሱን ከለላ አድርጎ ከመጣ የነሱን ሰላም ሊያውክ የሚችል ኃይል እንደሆነ ታውቆ እነርሱም በውስጣቸው አቋርጠው እዛ ቦታ ላይ ሽብር ሊፈጥሩ የሚችሉ ኃይሎችን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር መቻል አለባቸው ሲሉም አቶ አሕመድ ለነዋሪዎች መልእክት አስተላልፈዋል።