ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መንግሥት በኢትዮጵያ ካሉ 13 የስኳር ፋብሪካዎች መካከል ዐሥር የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ይዞታ የማዞሩ ሂደት በጥንቃቄ እያከናወነ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ተቋማቱን ወደ ግል ይዞታነት የማዛወር ሂደት ላይ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር ብሩክ ታዬ፤ በስኳር ፋብሪካዎቹ ወቅታዊ ቁመና ላይ ቴክኒካል ምዘና ማድረግ እና ፋብሪካዎቹ ወደ ግል ይዞታነት በሚቀየሩበት ወቅት ሊኖር የሚገባው የስኳር ገበያ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ የገበያ ስትራቴጅ እንደተጠናቀቀ አስረድተዋል።
በታቀደው መንገድ ወደ ዘርፉ የሚገቡ የግል ተቋማትን መደገፍ የሚቻልባቸው አሠራሮች በእስካሁኑ ሂደት እንደተጠናቀቀ የተናገሩት ዶክተር ብሩክ፤ ፋብሪካዎቹ በቀጣይ አቅም በተፈጠረላቸው ወቅት የሚኖራቸው ከባቢያዊ ተጽዕኖም ግምገማ ከግምት ተካቷል ብለዋል።
የስኳር ፋብሪካዎቹን ወደ ግሉ የማዛወር ሂደቱ ሁለት ዓመት ቢሞላውም እስካሁን ድረስ አንድም ወደ ግሉ ዘርፍ የተዛወረ ፋብሪካ አለመኖሩ ይታወቃል። ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እና በርከት ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ወሳኝ በመሆናቸው ሂደቱን ለመፈጸም ቁርጥ ያለ ቀን ማስቀመጥ እንደሚከብድ ዶክተር ብሩክ አስታውቀዋል።
ወደ ዘርፉ መቀላቀል የሚፈልጉ ተቋማት በጉዳዮ ዙሪያ መከወን የሚጠበቅባቸው የፋይናንስ እና ሎሎች ዝግጅቶች ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ያብራሩት ሚኒሴቴር ዴኤታው፤ ሆኖም በተቻለ አቅም ሂደቱን በሚፈለገዉ ፍጥነት ለማጠናቀቅ ማለቅ ያለባቸው ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የስኳር ፋብሪካዎቹን የመግዛት ወይም በጋራ የመሥራት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ለመለየት በተከናወነ የፍላጎት መጠየቂያ ጥናት እስካሁን 30 የሚደርሱ ተቋማት ዘርፉን መቀላቀል እንደሚፈልጉ ተረጋግጧል።
ከወራት በፊት የስኳር ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ይዞታነት በማሽጋገሩ ሂደት የሚመለከታቸውን የመንግሥት ተቋማት የሚያማክር ድርጅት የመቅጠሩ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ብሩክ፤ መተሀራ፣ ፊንጫ እና ወንጅ ስኳር ፋብሪካዎች ለጊዜው በመንግሥት ሥር የሚቆዮ ሲሆን፣ ወልቃይት፣ በለስ 1 እና 2 ፣ ቀሰም እና ሌሎች ቀሪ ፋብሪካዎች በመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ግል ይዞታነት ለማሸጋገር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።