ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሠራተኛ ማኅበራት ተወካዮች ኤጀንሲዎች የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን ባከበረ መንገድ እየሠሩ አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራዊ ኮንፌደረሽን (ኢሰማኮ) የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ላይ ስለሚሠሩበት የአሠራር ሂደት ከሠራተኛ ማኅበራት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ውይይት ማካሄዱ ታውቋል።
በተለይም “የግል ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሕግ እና አሠራርን ተከትለው አይሠሩም፣ ፍትሀዊ እና ግልፅ አይደሉም፣ የሠራተኞች መብት አይጠብቁም፣ እንዲሁም ዘመናዊ የጉልበት ብዝበዛ አስፈፃሚዎች ናቸው” ሲሉ ከተለያዩ የሠራተኛ ማኅበራት የተወጣጡ ተወካዮች ቅሬታቸውን በውይይቱ ላይ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራዊ ኮንፌደሬሽን የ20/80 አከፋፈልን ማስፈፀም እና የሠራተኞች መብት መከበር ላይ መሥራት እንዳለበት ያመለከቱት ተወካዮቹ፣ የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በአንቀፅ 171/1/ተ እና በአንቀፅ 174 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ያወጣውን መመሪያ ታች ድረስ ወርዶ እንዲያስፈጽምላቸው ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በሠራተኞች የሥራ ደህንነትን፣ መብት እና የአከፍፈል ሂደት ላይ የወጣው ህግ እና መመሪያ ይከበርልን ያሉት የማህበራቱ ተወካዮች፣ ጥያቄዎቻችን ለሚመለከተው የመንግሥት አካላት እንዲደርሱላቸውም በውይይቱ ላይ ሀሳብ ማቅረባቸው ታውቋል። ሲ
በቀሪው የዓለም ክፍል እንደሚታየው የኤጀንሲ አሠራር በኢትዮጵያ የእድገት ደረጃ ተመጣጣኝ ውጤት ያመጣል ማለት ተገቢ አለመሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎች፤ ኤጀንሲዎች በሚያደርሱት በደል እና የመብት ጥሰት ከማስጠንቀቂያ በዘለለ ተገቢ ቅጣት ይሰጣቸው ሲሉም አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል
የኤጀንሲው አሠራር በሌላው ዓለም ውጤታማ ሆኖ በኢትዮጵያ ክፍተት የተፈጠረው የወጡት መመሪያዎች በትክክለኛው መንገድ ተግባራዊ ስለማይሆኑ እንደሆነ የተናገሩት የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ መመሪያው እንዲወጣ ብሎም በኤጀንሲዎች የአሠራር ሂደት ላይ መተዳደሪያ እንዲረቅ የተደረገው በትግል ነው የሚል አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል።