ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከፍተኛ ገንዘብ የተመደበለት የጎዴ ቀላፎ፣ የጎዴ ሐርገሌ መንገዶች ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀመረ።
ዶክተር ዐቢይ ከም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ጋር ዛሬ ጎዴ ከተማ በመገኘት ነው የግንባታው መጀመር እውን መሆንን ያበሰሩት።
የመንገድ ግንባታው ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበትም ተነግሯል።
ግንባታው የተጀመረው መንገድ ከ270 ኪ.ሜ በሚበልጥ ርዝማኔው የጎዴ – ቀላፎ ሎት-1፣ የጎዴ – ሐርጌሌ ሎት እና የያአሌ – ዳና ሎት – 3 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ያካተተ ሲሆን፣ ግንባታው በ4 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ አስነብበዋል።
መንገዱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከማገናኘት ባሻገር፣ የጎዴ ከተማን የልማት ማዕከል ለማድረግና የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።