ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ለማውረድ ሁለቱ ክልሎች በመንግሥትና በሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ መነጋገር ይቀጥላሉ ተባለ።
በሶማሌ ክልል ምክትል የኮሚኒኬሽን ሓላፊ የሆኑት ዲባ አሕመድ ፤ በሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ማክሰኞ እለት 10 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከሰኞ ጀምሮ የሞቱት ሰዎች ባጠቃላይ 27 መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።
በሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢ ያለው ከሁለት ዓመት በላይ የቆየና ብዙ ሰው የሞተበት የድንበር ግጭት እንደሆነ የተናገሩት ሓላፊው፤ የዚህ ሳምንት ክስተት ግን ከቀደሙት የተለየ እንደነበር ገልጸዋል።
ጥቃቱን በተመለከተ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት አመራሩ ትናንት የአፋር ክልል ባለሥልጣናት አሸባሪ ቡድን በሚል ጥቃቱን ያስቀመጡበት ሁኔታ እንዳልተመቻቸው ከመናገራቸው ባሻገር በእርግጥ የሽብር ጥቃት በሚመስል መልኩ ዐሥር ንጹሀን ዜጎች ቢገደሉም እስካሁን ድረስ ግን አሸባሪ ኢትዮጵያ ውስጥ አላየንም ብለዋል።
“እኛ በመነጋገር እናምናለን፤ የአፋር ወንድሞቻችንም ያምናሉ ብዬ ነው የማስበው፤ ንግግሩም ይቀጥላል” ያሉት ሓላፊው መሰል ችግሮችን ለመፍታት ቀደም ባለው ጊዜም የሶማሌ ክልል ከአፋር ክልል ጋር ሠፊ ውይይት ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸዋል።
ምክትል የኮምንኬሽን ኃላፊ የሆኑት ዲባ፤ ጥቃቱን ማን እንዳደረሰ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸው፤ “ሕዝቦቹ ወንድማማች ናቸው። ሁከት የሚፈጥር ሦስተኛ አካል አለ ብዬ ነው የምገምተው። ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደረግ አካል አለ። መጀመሪያም ክስተቱ እንዲፈጠር እቅዱን ዘርግተው አሁንም ሰላም እንዳይኖር ንቅናቄ እያደረጉ ነው” ብለዋል።
የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ተመሳሳይ ባህል እንዳላቸው እንዲሁም በጋብቻም ተሳስረው እንደሚኖሩ በማጣቀስ፤ “ለፖለቲካ ፍጆታ ብለው በልቶ ጠጥቶ ያላደረ ሕዝብ ማጫረስን በምን እንደምገልጸው ራሱ አላውቅም” ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን በአካባቢው ሰላም የሰፈነ ሲሆን በፌደራልና በክልል ደረጃም ንግግር ተጀምሯል። በተጠቀሰው ቦታ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ400 ያላነሱ ሰዎች እንደተገደሉ እና ከፍተኛ ንብረት እንደወደመም መረጃዎች ይጠቁማሉ።