በሺኅዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ትግራይ ውስጥ በርሃብ እና በመጠለያ እጦት እየተሰቃዮ ነው

በሺኅዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ትግራይ ውስጥ በርሃብ እና በመጠለያ እጦት እየተሰቃዮ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ወደኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኛ ኤርትራውያን ከፍተኛ መድልዎ እየደረሰብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በመቶ ሺኅዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ያሉ ሲሆን፣ ወታደሮችና የመንግሥት ሠራተኞች ያልሆናችሁ ወደ ስደተኞች ካምፕ አትገቡም በሚል እንደተከለከሉ በመናገር ላይ ናቸው።
ከኤርትራ በተለያዩ ምክንያቶች ጠፍተው የመጡና የኢትዮጵያ ድንበርንም አቋርጠው የገቡ ስደተኞች፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በሚገኙ የድንበር ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ቢሆንም ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ መልኩ ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአዲግራት፣ ዛላምበሳ፣ ሽራሮ፣ ዓዲ ነብር፣ ራማ እና ገርሁ ስርናይ በሚባሉት ከተሞች ትምህርት ቤቶች ውስጥ ስደተኞቹ ተጠልለው የሚሆነውን በስጋት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
ቀደም ሲል በነበረው አሠራር መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች በድንበር አካባቢ በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እንዲቆዩ ሲደረግ ቢቆይም፤ ከባለፈው አመት ጥር ወር ጀምሮ እነዚህ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከላት በመዘጋታቸው፤ የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ጉዳዮች ኤጀንሲ ሠራተኞች ኤርትራውያን ወደሚገኙበት የለይቶ ማቆያ ቦታ በመሄድም የምዝገባና የማጣራት ሥራ እያካሄዱ መሆናቸው ታውቋል።
ስሟን ያልገለጸች የ22 ዓመቷ ኤርትራዊ ከ18 አመት በላይ የሆናቸው ኤርትራውያን የብሔራዊ አገልግሎት አካል የሆነው የሳዋ ማሰልጠኛ ማዕከል መግባታቸው አስገዳጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም እርሷም ይህንን ስለማታምንበት ሸሽታ ወደ ኢትዮጵያ መሰደዷን ትናገራለች።
“ዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ጉዳይ የሚመለከተው ተቋም ሁሉንም ስደተኞች በእኩል እንደሚያይ ነበር የምናውቀው። እዚህ ከመጣን በኋላ ግን መድልዎ እንደሚፈፀም እየተመለክትን ነው:: ወታደሮችን ለይተው ሲወስዱ አይተናል:: እኛም ውትድርናን ሸሽተን ነው የመጣነው” ያለችው ወጣቷ፤ እስካሁንም ባለው ወቅት የዓዲግራት ሕዝብ ቁርስ፣ ምሳና እራት እያቀረበ የመገባቸው ቢሆንም በባለፉት ሁለት ቀናት ግን ይሄ በመቋረጡ ለርሀብ መጋለጣቸውን አስታውቃለች።
ከምንም በላይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ስደተኞቹ የተጠለሉበት ኮሌጅ ትምህርት ለመጀመር ፅዳት እያካሄደ መሆኑ ደግሞ መውደቂያችን የት ይሆን? የሚለው እንዳሳሰባቸውና ክፉኛ እንዳስጨነቃቸው እየተናገሩ ነው።

LEAVE A REPLY