የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ የነበሩት እነቀሲስ በላይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ተገዢ ሆኑ

የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ የነበሩት እነቀሲስ በላይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ተገዢ ሆኑ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ራሳቸውን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ  አድርገው በነበሩት በእነቀሲስ በላይ መኮንን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል እየተካሄደ የነበረው የእርቅ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል ተባለ።

የእርቅ ሂደቱን ሲመሩ የነበሩ ሽማግሌዎች ዛሬ ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ. ም በሰጡት መግለጫ፤ መጀመሪያ ቋሚ ሲኖዶስ፣ በመቀጠልም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ባጸደቀው መሠረት የእርቅ ሂደቱ ተጠናቋል ሲሉ ይፋ አድርገዋል።
የኦሮሚያ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መዳከም ያሳሰባቸው ወገኖች ችግሩን ለመፍታት በሚል የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አቋቁመው ነበር ሲል ያስታወሰው መግለጫ፤ “የተነሱት ችግሮች እንዳሉ በአባቶች፣ ሊቃውንትና ምእመናን ቢታመንም መፍትኄው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት መቋቋም ነው ወይ የሚለው በአባቶች እና በምእመናን ዘንድ መከፋፈል ፈጥሮ ቆይቷል” ብሏል።
በክልሉ አለ የሚባለውን የአገልግሎት መዳከም፣ በቋንቋው የሚያስተምሩ በቂ አገልጋዮች አለመኖር እና ሌሎችም የአስተዳደር ችግሮች እንዴት ይፈቱ የሚለውን በውይይት ለመፍታት የተቋቋመው የሽማግሌዎች ቡድን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አመራሮችን፣ ቋሚ ሲኖዶሱን እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን ሲያነጋግር መቆየቱ ተሰምቷል።
 ለሥድሥት ወራት ችግሩን ለመፍታት ውይይት ሲካሄድ እንደነበር የተናገሩት አስታራቂ ሽማግሌዎች “በኦሮሚያ ያጋጠመው የአገልግሎት መዳከም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር በሚቋቋም ጠንካራ አካል በኩል በአንድነት መፍታት የተሻለ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ታምኖበታል” በማለት የተደረሰበትን ውጤት አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ያጋጠመው የአገልግሎት መዳከም የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት በኦሮምኛ ቋንቋ የሚሰጠው አገልግሎት እጅግ በተጠናከረ መልኩ ለማካሄድ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች አንድ ሆነው እንዲነሱ የአደራ ጥሪ መቅረቡም ታውቋል።

LEAVE A REPLY