ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመምህርነት ሙያ ከዘር፣ ከብሄርና ከወገንተኝነት ነፃ ሆኖ በከፍታ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ሙያ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ገለጹ።
“መምህራን ቀውስ ለመቀልበስም ሆነ ለመጪው ጊዜ ብሩህነት ግንባር ቀደም ሚና አላቸው” በሚል ትምህርት ሚኒስቴር ፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት የመምህራን ቀን ዓመታዊ በዓል አውደ ጥናት በአማራ ክልል ርዕሰ መዲናዋ እየተካሄደ ነው።
በዚህ አውደ ጥናት የመምህርነት ሙያ ላይ እና በኮቪድ 19 ተፅዕኖ ላይ የመምህራን ሚናን የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ፤ አሁን እየታዩ ያሉ ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ግብረ ገብነት ያለው፣ ብዝሀነትንና አንድነትን የሚያስተናግድ ትውልድ ለማፍራት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
“የያዘነው የትምህርት ሙያ ከዘር፣ ከብሄርና ከወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ከፍ ብሎ የሚገኝ ግዙፍ ሙያ ነው” በማለት የተናገሩት የትምህርት ሚኒስትሩ፣ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ መምህራን ትልቅ ሓላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የመምህራን ክብር በሚከፈሉት ክፍያና በሚኖሩት ኑሮ የሚለካ ሳይሆን ሙያው በራሱ ክቡር የሚሰጠው ነው ያሉት የአማራ ክልል የሠራተኛ ጉዳዮ ሓላፊ፤ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው፣ “ሁላችንም የመምህራን የእጅ ሥራ ውጤት ነን ፣ የትምህርት ዘርፉ ለሀገር እንዲጠቅም ለማድረግም የመምህራንን ጥቅም ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል” ሲሉ ተናግረዋል።