ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ጸብ ቀስቃሽ አስተያየት በመቃውም ለተቃውሞ ሠልፍ አደባባይ ወጡ።
እነዚህ በዩናትድ ኪንግደም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የትራምፕን አስተያየት በመቃውም ለንደን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ነው ሠልፉን ያካሄዱት።
ሱዳን እና እስራኤል የሰላም ስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሀውስ የሁለቱን ሀገራት መሪዎች ጋዜጠኞች በተገኙበት በስልክ ሲያነጋግሩ፤ “ግብፅ የሕዳሴ ግድቡን ልታፈነዳቸው ትችላለች” ሲሉ መደመጣቸው አይዘነጋም።
ይህ ሓላፊነት የጎደለውና ህገ ወጥ ጣልቃ ገብነት በታየበት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ንግግር የተበሳጩ ኢትዮጵያውያን “የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኔ ነው” ፣ “አሜሪካ ገለልተኛ አይደለችም” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ሠልፍ ወጥተዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ለግዴለሽ ንግግራቸው ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል ያሉት ሠልፈኞቹ፤ ” ዶናልድ ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ የሰጡትን አስተያየት እንዲያስተባብሉ እና ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ ለማቋረጥ የወሰኑትን ዳግም እንዲያጤኑት እንጠይቃለን” ብለዋል።