ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲ አበባ ጤና ቢሮ ሥር በሚተዳደሩ እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በተቋቋሙ የሕክምና መስጫዎች ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች፣ በተለያየ ጊዜ የተገባላቸው ቃል እንዳልተፈጸመላቸው በመግለፅ በድጋሚ ቅሬታቸውን አሰሙ።
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ መንግሥት በሕክምና ባለሙያዎችን ላይ የሚኖረውን ጫና ከግምት በማስገባት ከባለሙያዎቹ ጎን እንደሚቆም መግለጹ አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎ የሚንስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 14/2012 ዓ. ም ባካሄደው 83ኛ መደበኛ ስብሰባ የኮቪድ-19 ወረርሽንን በመከላከል እና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ባለሙያዎች ልዩ አበል እንዲከፈላቸው ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
ምክር ቤቱ እንደሙያቸው እና ሥራቸው ሁኔታ ከ1ሺህ150 ብር ጀምሮ እስከ 300 ብር በየቀኑ እንዲከፈላቸው በመወሰኑ፤ በፌደራል ደረጃ የሚተዳደሩት እንደ ኤካ ኮተቤ፣ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ሚሊኒየም ሆስፒታል ያሉት የጤና ተቋማት እና አንዳንድ ክልሎች ወሳኔውን መሠረት በማድረግ ለባለሙያዎቻቸው ልዩ አበል እንደከፈሉ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሥር ከሚተዳደሩ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች መከካከል የተወሰኑት የኮሮናቫይረስ ሕክምና መስጫ ማዕከል ሆነው እያገለገሉ ቢሆንም ለባለሙያዎች እስካሁን ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው የጤና ባለሙያዎቹ በድጋሚ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ግንቦት አጋማሽ መመሪያው ከወጣ በኋላ የባለሙያ እና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የአበል ዝርዝር በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ደረጃ አልወጣ ሲል ጠብቀን መታገል ጀመርን” ያሉት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የጉቶ ሜዳ ኮቪድ -19 ማዕከል ሠራተኛ የሆኑት አቶ ዲኖ ጀማል፤ ቅሬታቸውን በተገቢው መንገድ ለማቅረብ ይረዳቸው ዘንድ ከእያንዳንዱ የኮቪድ -19 ሕክምና ማዕከል 3 ተወካይ በመምረጥ አቤቱታቸውን ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እንዳስገቡ አረጋግጠዋል።
በአበል ክፍያ ተጸፈጻሚነት ጥያቄ ሂደት ላይ ወኪሎቻቸውን ያላሳወቁትን ሳይጨምር 1 ሺኅ 158 ሠራተኞች ወኪሎቻቸውን መርጠው ልዩ አበሉ ለምን እንዳልተከፈላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም እስካሁን ክፍያው ሳይፈጸምላቸው ቀርቷል።
እነዚህ የጤና ባለሙያዎች ጉዳያቸውን በተመለከተ የጤና ሚኒስቴርን ባነጋገሩበት ወቅት ሳይከፈል የቆየው የአበል ገንዘብ ተጠራቅሞ ሁለት ቢሊየን ብር በመድረሱ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ይህን ማድረግ እንደማይችልና ጥያቄው እንደማይመለከተው የገለጸላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።