ሽመልስ አብዲሳ በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈረስም...

ሽመልስ አብዲሳ በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈረስም አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሀገራችን ሕዝቦች ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለፍትሀዊ ተጠቃሚነት በጋራ እየታገሉ መስዋእትነት  እየከፈሉ በጋራ ተጉዘዋል፣ አሁንም በመጓዝ ላይ ይገኛሉ ያሉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ በሀገሪቱ በመጣው የለውጥ ሂደት በሕዝቦች ትግል ድል የተነሱት  ጨቋኝ ክንዳቸው እንዲሰበሰብ፣ የብዝበዛ መረባቸው እንዲበጣጠስ የተደረገው ሴረኛው የወያኔ ቡድን አሁንም የተካነበትን ሴይጣናዊ የተንኮል ተግባሩን በንጹሀን ላይ እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

የወያኔው ቡድን ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ደም በማፋሰስ፣ በሚፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከቻለ ከተገፋበት የማዕከል ሥልጣን መመለስ፣ ካልቻለ የሚመቸውን አሻንጉሊት መንግሥት ለማቋቋም በተለመደው አይነ ደረቅነቱ የቀን ቅዠት ውስጥ በመግባት ሌት ተቀን ሴራ በመጎንጎን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል።
” በተለይም ይህ ቡድን የኦሮሞና የአማራ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭት  ለመፍጠር መሞከር የሰርክ ተግባሩ ነው፡፡ ይህ ሙከራዉ አልሳካለት ሲለዉ የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድንን በማስታጠቅ የሎጀስቲክና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ በትሮይ ፈረስነት በመጠቀም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማስፈጸም  የሀገራችንን የለውጥ ተስፋ ለማጨለም እየተፍጨረጨረ ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ አሸባሪው የኦነግ ሸኔ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሕዝብና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች  ትብብር እየተወሰደ ባለው እርምጃ  በከፍተኛ ሁኔታ አከርካሪው ተመትቶ በመንኮታኮት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ይህ በሕዝብና በጸጥታ አካላት ክፉኛ እየተመታ ያለው  ቡድን ተስፋ ወደ መቁረጥ በመግባቱ፣ እንዲሁም ከወያኔ የሚሰጠውን ተልዕኮ በመውሰድ ሰላማዊ ዜጎችን አርሶ አደሮችን፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች ላይ የሽብር ጥቃት ወደ መሰንዘር ተሸጋግሯል በማለት የኦነግ ሸኔን ድርጊት ያጋለጡት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ይህ ታጣቂ ኃይል በትላንትናው ዕለት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለው  ቀበሌ ንጽሃን ሰዎች ላይ የሽብር ጥቃት በማድረስ በሰው ህይወት እና አካል ላይ ጉዳት ማድረሱንም አውግዘዋል።
“በዚህ የሽብር ጥቃት  ዉድ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽኩ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት አጥብቄ አወግዛለሁ” ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በዚህ አጋጣሚ በኦነግ ሸኔ  አሸባሪ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው ውጤታማ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፣ በኦነግ ሸኔና ወያኔ የጥፋትና ሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈራርስም ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ነፍጠኛን አከርካሪውን ሰብረናል በማለታቸው ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸው እንደነበር አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY