ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ትናንት በምዕራብ ወላጋ የተገደሉት የአማራ ተወላጅ የሆኑት ንጹሐን ዜጎች ለስብሰባ በተጠሩበት ስፍራ እንደሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ተደጋጋሚ የአንድ ብሔር ተኮርና የሃይማኖት ጥቃት እየተፈጸመበት ያለው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመው የትናንቱ ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉንም በይፋ አረጋግጧል።
የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ጌታቸው ጥቃት አድራሾቹ በሐሰተኛ መልኩ ነዋሪዎች ለስብሰባ ከሰበሰቡ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ በተወረወረባቸው ቦምብ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“በኦነግ ሸኔ ስም የሚንቀሳቀስው ቡድን ትናንት በስበሰባ ስም ሰዎችን ከሰበሰቡ በኋላ ቦምብ ወርውረውባቸው ጉዳት መድረሱን የሚጠቁም መረጃ ነው ያለን” በማለት በወለጋ በሚኖሩ አማሮች ላይ የተደረገውን ዘር ተኮር ጥቃት የገለጹት ሓላፊው፤ “ሕዝብ በአንድ ቦታ ሰብስቦ በቦምብ ማቃጠል ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም። ጥቃቱ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ትናንት እሁድ ጥቅምት 22 ቀን ጥቃቱ የተፈጸመው ከምሽቱ 12 ሰዐት አካባቢ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ቦምቡን ንጹሃን ዜጎቹ (የአማራ ተወላጆች) ላይ የወረወሩት ሐሰተኛ ስበሰባ የጠሩት መሆናቸውንም አረጋግጠናል ብለዋል።
በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ያልሸሸጉት አቶ ጌታቸው፤ መረጃ አጣርቶ የሚልክ ቡድን ወደ ሥፍራው እንደተላከ በመጠቆም እስካሁን በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።
“የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ እየተጠቀሰ ነው። ነገር ግን ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ በአካባቢው ያለው አካል አጣርቶ እስኪልክልን እየተጠባበቅን ነው” በማለት የደረሰውን አደጋ መጠን ሸፋፍነው ለማለፍ የሞከሩት እኚህ የክልሉ ባለሥልጣን በስፍራው ቀደም ሲል በምሽት እንዲህ ዓይነት መሰል ስብሰባዎች ስለመካሄዳቸውም ሳይገልጹ
ቀርተዋል።