ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በምዕራብ ወለጋ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ አካላት የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ የሐዘን መልእክት አስተላለፉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጡት መግለጫ፤ አሁን በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን ብሔር ተኮር ጥቃት በፍጥነት ለማስቆም መንግሥታቸው አስፈላጊውን መንገድ ሁሉ እንደሚጠቀም አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዮን አስመልክቶ የሰጡትን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፦
በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልፃለሁ።
የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።
ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የሚያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ እርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።
መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።
የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።
ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።
መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።
ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት።፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።