ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በምዕራብ ወለጋ ዞን፤ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በአማራ ብሔረሰብ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸም የተጀመረው ቅዳሜ ዕለት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
” ቅዳሜ ዕለት ልክ መከላከለያ እንደወጣ ኦነግ ሸኔ ገባ። ከዚያ ወረራና ዘረፋ ጀመረ። ቅዳሜ እንደዛ እያደረጉ አደሩ። ሞባይል ስልክ፣ ገንዘብ እንዲሁም የቤት እቃ ወስደዋል። ትናንት (እሁድ) 11 ሰዐት አካባቢ ስብሰባ አለ ብለው አዛውንት፣ ሴቶችና ሕጻናት ሳይለዩ ሰብስበው አንድ ትምህርት ቤት አስገቡ፤ ከዚያም ጥቃት ፈፀሙ።” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ ዘግናኙን ጥቃት የፈጸመው ስብሰባ የጠራቸው የኦነግ ሸኔ ቡድን መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ጥቃቱ ሲፈጸም ከሌሎች ሰዎች ጋር ሸሽተው ጫካ የገቡት እኚህ የአካባቢው ነዋሪ፤ “ሰዉ በፍርኃት ተገዶ ነው ወደ ስብሰባው የገባው። ሕይወቱ የሚተርፍ መስሎት ነው የሄደው። ከዚያ ግንበመትረየስና በቦንብ ጥቃት ተፈፅሞበታል” ብለዋል።
“የሚፈልጉት ወንዶችን ነበር። እኛ ሸሽተን ጫካ ውስጥ ነበርን። ሴቶች፣ ሽማግሌዎች ቤት ቀርተዋል፤ ገንዘብ ቢውስዱ እንጂ እነርሱን አይነኩም ብለን ነበር ያሰብነው። ከዚያ የፍንዳታ ድምፅ ስንሰም ቀስ ብለን ከተደበቅንበት ጫካ ወጥተን ስናይ አመድ ሆነዋል።” ያሉት የዐይን እማኙ፤
ሰኞ (ዛሬ) ከረፈደ በኋላ መከላከያና ልዩ ኃይል መግባቱን ተከትሎ ከሌሎች የሸሹ ሰዎች ጋር ካደሩበት ጫካ መውጣታቸውን ገልጸዋል።
“አንድ ወንድሜ ሞቷል፣ የአጎቴ ልጅና አባቱ ሞተዋል። ወንድሜ ሚስትና ልጆች አሉት። አጎቴ ደግሞ ሽማግሌ ነበር። ወንድሜ ስብሰባ ሲጠራ ልጆቼን ልይ ብሎ ከጫካ ወጥቶ ሄዶ ነው የሞተው። ሚስትና ልጆቹም አብረው አለቁ።” ሲሉ የጥቃቱን አስከፊነት ያጋለጡት የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪ፤ አሁን መከላከያ ከገባ ወዲህ በሥፍራው መረጋጋት መኖሩን፣ ሠራዊቱ የሸሹትን ወደ ቀዬአቸው እየጠራ እንደሆነና የሞቱ ሰዎችን ሬሳ እየሰበሰበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
እስካሁን ድረስ 54 ሰዎች መሞታቸውን ማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት እኚህ የዓይን እማኝ፤ በሦስት ቀበሌዎች ከደረሰው ጥቃት አኳያ ተጨማሪ መረጃ መሰብሰቡን ተከትሎ 60 ሰው ሕይወቱ ማለፉንና 20 ሰዎች ደግሞ መቁሰሉን የሚያሳዮ ፍንጮች መገኘታቸውን አያይዘው ገልጸዋል።