ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዛሬ የያዛቸውን አጀንዳዎች እንዲወያይባቸው በአፈ ጉባኤው በኩል የቀርበለትን አጀንዳ ውድቅ በማድረግ እየተከናወነ ባለው ብሔር ተኮር ጥቃት ላይ ብቻ እንደሚወያዮ በመናገር እምቢተኝነታቸውን አሳዮ።
ለዕለቱ የተያዘላቸውን አጀንዳ ውይይት ከመጀመራቸው በፊት ከ2 ሰዐት በላይ ስለዚሁ ጉዳይ በእንባ እየተናነቃቸው ጭምር ሀሳባቸውን በስሜት የገለጹት የፓርላማ አባላት፤, “በመግለጫ መፍትኄ አይመጣም፣ ድርጊትና እርምጃ ያስፈልጋል፣ ዛሬ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየተጨፈጨፉ ዝም ካልን ነገ በሺዎች የሚቆጠሩ እንዲጨፈጨፉ መፍቀድ ነው” ሲሉ በእምቢተኝነታቸው ፀንተዋል።
ዛሬ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ በጥቃቱ ላይ የመንግሥትን አቋም የሚያንጸባርቅ መግለጫ አንብበው፣ የ1 ደቂቃ የህሊና ጸሎት ከተደረገ በኋላ ወደ ዕለቱ አጀንዳዎች ለመገንባት ማስተዋወቅ ሲጀምሩ፣የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት እዚህም እዛም እጅ እያወጡ ተራ ሳይጠብቁ አካሄዱን ተቃውመዋል።
በዜጎች ላይ የብሔር ማንነትንና ሃይማኖትን መሰረት ባደረገ ጥቃት በየጊዜው እየተጨፈጨፉ በምን ሞራል ነው ሌላ አጀንዳ ላይ የምንነጋገረው? ያሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት ሰላም ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስትር እና ሌሎችንም የሚመለከታቸው አካላት መጥተው ማብራሪያና ምላሽ እንዲሰጡን እንፈልጋለን ሲሉ ተሰምተዋል።
አልሸባብና አይ ኤስ ኤስን ለመመከት በሰው አገር ጭምር ሰላም የሚያስከብረው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ እውን ኦነግ ሸኔን ማሸነፍ አቅቶት ነው ወይ? ከ2 ዓመት በፊት በለውጥ ስሜት ሥራ ስንጀምር የነበረን ተስፋና ሞራል አሁን የለም፤ ሲሉ በስሜትና በእንባ ታጅበው ሀሳባቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
“መንግሥት ጥቃት በተፈፀመ ቁጥር፣ ይህን ያደረገው እገሌ ነው እያለ በተደጋጋሚ መግለጫ ሰጥቷል፤ ጠላት ነው የተባለው ከታወቀ ለምን የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አልተቻለም ያሉት የፓርላማው አባላት በፍጥነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በጉዳዮ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።