በአማራ ክልል ሶሮቃና ቅርቃር በሚባሉ አካባቢዎች የህወሓት ጥቃታ በአማራ ልዮ ኃይል ከሸፈ

በአማራ ክልል ሶሮቃና ቅርቃር በሚባሉ አካባቢዎች የህወሓት ጥቃታ በአማራ ልዮ ኃይል ከሸፈ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ትናንት ምሽት 4፡30 ጀምሮ በአጠቃላይ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ካምፖች፣ ዴፖዎች፣ እና የተለያዩ መሠረተ ልማት ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የተቀናጀ ጥቃት ማድረስ መጀመሩን የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል አዛዦች እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ የጀመሩት የጥፋት ጉዞ አሁን ደግሞ ወደጥቃት መሸጋገሩን አቶ ተመስገን ጥሩነህ አረጋግጠዋል።
ሠራዊቱ ያለውን ትጥቅ ወደ መቀማት ሄዶ እንደነበር የተናገሩት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት፤ በአማራ ክልልም ሶሮቃ እና ቅራቅር በሚባሉ አካባቢዎች የጥቃት ሙከራ ማድረጉን፣ እንዲሁም በክልሉ ልዩ ኃይል መመከቱንም ይፋ አድርገዋል።
 በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎችም ሊገመት የሚችል ጥቃት በቀጣይ እንደሚኖር ግምታቸውን ያስቀመጡት አት ተመስገን ጥሩነህ ፤ የአማራ ልዩ ኃይል አንዳንድ በትግራይ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ አባላት ከበባ ውስጥ የነበሩ የመከላከያ አባላትንም ማዳንና ማውጣት መቻሉን አስረድተዋል።
ልዩ ኃይሉ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የከባድ መሳሪያዎችንም ከስፍራው በማውጣት ተመልሰው ለውጊያ እንዲዘጋጁ ማድረጋቸውን የተናገሩትና የኮማንድ ፖስቱን ከመከላከያ ጋር በመሆን በቅንጅት እየመሩና እየሠሩ ያሉት  አቶ ተመስገን “የአማራ ሕዝብ ስትራቴጂካዊ ጠላቱን እስካላጠፋ ድረስ በየጊዜው የሸረሪት ድር ስናፀዳ አንኖርም” ሲሉም ተደምጠዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በህወሓት የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የሥልጠና ድጋፍ የሚደረግለት ነው የሚሉት ርዐሰ መስተዳደሩ፤ በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ የኤርትራ ወታደር አይነት ልብሶችን በመስፋትና የትግራይን ልዩ ሀይል በማልበስ ለትግራይ ሕዝብ “ኤርትራ ወረረችህ” በማለት ሕዝቡን እያደናገረ ይገኛልም ብለዋል።
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይህንን ኃይል ሥርዓት የማስያዝ ሥራ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመሆን የክልሉ መንግሥት እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ሁሉም የፀጥታ ኃይል የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ የሚመጣውን ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ እንዲሆንም አሳስበዋል።

LEAVE A REPLY