ከሌሊት ጀምሮ በትግራይ ኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ

ከሌሊት ጀምሮ በትግራይ ኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጦርነት በተጀመረባት በትግራይ ክልል ከትናንት ሌሊት ጀምሮ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መቋረጡ ታወቀ።
ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ደግሞ ኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መቋረጡን ይፋ ያደረገው በኢንተርኔት ነፃነት ላይ የሚሠራው ኔት ብሎክስ የተሰኘው ተቋም ነው።
በአሁኑ ሰዐት የትግራይ ክልል ቴሌቪዥንም ሆነ ድምፂ ወያነ የሚሠሩ ሲሆን የተለመደ ፕሮግራማቸውን እያስተላለፉ መሆናቸው ታውቋል።
ከትናንት ምሽት አንስቶ በትግራይ ክልል ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሎች ሲንቀሳቀሱ እየታየ የነበረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዛሬው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ክልሉን በሚያስተዳድረው ህወሓት ላይ ጦርነት መከፈቱን አረጋግጠዋል።
ትናንት ሌሊት አምስት ሰዐት አካባቢ በመቀሌና ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኩዊሃ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ቢቢሲ ቢዘግብም እስካሁን ድረስ ከትግራይ ክልል በኩል ምንም አይነት ይፋዊ መረጃ አልተገኘም።
የህወሓቱ ከፍተኛ አመራር ጌታቸው ረዳ ትናንት ሌሊት “ወንድምና እህቶች ተረጋጉ” የሚል መልእክት በፌስ ቡክ ገጻቸው ያስተላለፉ ሲሆን፣ ዶክተር ደብረፂዮን ደግሞ ልክ የሌላ ሀገር ወራሪ የመጣ ይመስል የትግራይ ሕዝብን ተነስ ሲሉ ቅስቀሳ ማካሄዳቸው ታውቋል።

LEAVE A REPLY