ጠ/ሚ/ር ዐቢይ “ጡት ነካሽ” ባሉት ኃይል ላይ መከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን...

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ “ጡት ነካሽ” ባሉት ኃይል ላይ መከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን ይፋ አድርገዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በህወሓት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ አሉ።

“ይህንን ጡት ነካሽ ኃይል ለማሳፈር እና ለመደምሰስ አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን እገልጻለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ መከላከያ ሠራዊት አገር የማዳን ግዳጅ እንደተሰጠውም በይፋ አረጋግጠዋል።
 “ህወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል፣ ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል” በማለት ህወሓት በይፋ ጦርነት መጀመሩን ያጋለጡት ዶክተር ዐቢይ፤ ሠራዊቱ ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ መሆኑን ጠቁመው፣ ጦሩ በቦታው የሚገኘው የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
“ህወሓት እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል” ሲሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ያጋለጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል” በማለት ህወሓት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ አጋልጠዋል።
በሌላ በኩል የትግራይ ክልል መንግሥት በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት በትግራይ ላይ የኃይል እርምጃ ወደ መውሰድ እየተሸጋገረ ነው የሚል መግለጫ መሰጠቱ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY