ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኘው መከላከያ ሠራዊት እየወሰደ ያለው እርምጃ ግልጽ፣ የተወሰነ እና ሊደረስበት የሚችል ዓላማ ያለው ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
“በፌዴራል መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግልጽ፣ የተገደበ እና ግቡን የሚመታ ዓላማ ያለው ነው” በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም የሕግ የበላይነትን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያውያንን መብት በማስጠበቅ ፣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሰላማቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ለማድረግ ነው ብለዋል።
መንግሥት ከህወሓት አመራሮች ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በሽምግልና ለመፍታት ለበርካታ ወራት በትዕግሥት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት ዶክተር ዐቢይ፤ ይሁን እንጂ በወንጀለኛው የህወሓት ቡድን ሁሉም የሰላም ጥረት ውድቅ ለመሆን መገደዱንም አስረድተዋል።