አዲስ አበባ በመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ በየአመቱ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን...

አዲስ አበባ በመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ በየአመቱ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ በጥናት ተረጋገጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከ400 በላይ ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባ ከተማ ከፍርድ ቤት እግድ ጋር በተያያዘ ለመቆም መገደዳቸው ተሰማ።

በመዲናዋ ያለውን የመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታን በሚመለከት  እየተካሄደ ባለው ውይይት ህገወጦች ከፍርድ ቤት የሚያወጡት እግድ ህገ ወጥነትን ለመከላከል ከባድ ፈተና ሆኗልም ተብሏል።
እንዲህ አይነቱ ነገር የፍርድ ቤቶች የእግድ አሰጣጥ ላይ ጥልቅ ምርምር የማድረግ ክፍተት በመኖሩ እንደሆነ በተነሳበት የውይይት መድረክ ላይ፤ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ  በፍርድ ቤት እግድ ምክንያት ከ400 በላይ የከተማዋ ፕሮጀክቶች እንደቆሙና ከነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የመንገድ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ህገ ወጥነትን መከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ከንቲባዋ፤ የፀጥታ አካላት፣ ፍርድ ቤቶችና የመንግሥት አመራሮች ራሳቸውን ሊፈትሹና ይህን ህገወጥ ድርጊት መከላከል ላይ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
የመሬት ወረራንና ሕገወጥ ግንባታን መከላከል ካልተቻለባቸው ምክንያቶች መካከል የመሬት ሌብነት በመንግስት መዋቅር ውስጥ መኖር፣ የመሬት ወረራን በእምነት ተቋማት ስም ማከናወን፣ የሕግ ድጋፍ፧ አለመኖርና አመራሮች ለህገወጥ ግንባታ ካርታ እንዲዘጋጅ ማድረግበዋነኛነት እንደሚጠቀሱ በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ተገልጿል።
አዲስ አበባ ከተማ በመሬት ወረራና በህገ ወጥ ግንባታ ብቻ በየዓመቱ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እንደምታጣም የተደረገው ጥናት አረጋግጧል።

LEAVE A REPLY