ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የህወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ጦርነቱ ቆሞ ድርድር እንዲካሄድ መጠየቃቸው እየተነገረ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል መንግሥትና እና ትግራይ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ጦርነቱን እንዲያስቆም እና ከእርስ በእርስ ጦርነት አገሪቷን እንዲታደግ የተማፀኑት ዶክተር ደብረፂዮን፤ ለወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት በጻፉት ደብዳቤ ሁሉን አካታች የሆነ ውይይት እንዲካሄድ መጠየቃቸው ተረጋግጧል።
“ፖለቲካዊ ችግሮች በወታደራዊ አማራጮች እንደማይፈቱ ጽኑ እምነት አለኝ” ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ የገለፁት ደብረፂዮን፤ አሁን ላይ ጦርነቱ ቆሞ ወደ ድርድር እንዲገባ ህወሓት ፍላጎት እንዳለውም አረጋግጠዋል።
በተያያዘ ዜና የህወሓትና የትግራይ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ጦርነቱ ቆሞ ድርድር እንዲደረግ መጠየቃቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪልም ትናንት ምሽት በሠራው ዘገባ ላይ አረጋግጧል።
ህወሓት ለእርቅ ዝግጁ መሆኑን ይግለፅ እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው በፌደራል መንግሥቱ በኩል ለድርድር ፍላጎት የሌለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዶክተር ዐቢይ ትናንት ለውጪ ማኅብረሰቡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር መንግሥት የጀመረውን እርምጃ ያጠናቅቃል ያሉ ሲሆን፤ ከሁለት ቀናት በፊትም በትዊተር ገጻቸው ላይ “ወንጀለኛ አካላት እርቅ እና ድርድር ፈላጊ በመምሰል ከሕግ የበላይነት ሊያመልጡ አይችሉም። የሚከናወነው ኦፕሬሽን ዓላማው፣ የሚገባቸውን ቅጣት ሳያገኙ ከገደብ አልፈው የቆዩትን አጥፊ ግለሰቦች እና ቡድኖች በሀገራችን ሕግጋት መሠረት ተጠያቂ ማድረግ ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።