ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ ሰኞ ምሽት ዘግናኝ በሆነ መልኩ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ማግኘቱን አምንስቲ ኢንተርናሽናል ገለፀ።
በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ማይካድራ በተፈጸመው ጥቃት ቁጥራቸው በመቶዎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል ያለው አምንስቲ፤ በየቦታው ወድቀው የሚታዩ አስከሬኖችን የሚያሳዩ አሰቃቂ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን በመመርመር ምስሎቹ የቅርብ ጊዜና ስፍራውም ማይካድራ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደቻለ አስታውቋል።
በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ተዋጊዎች ሳይሆኑ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን ለማወቅ ቢቻልም ግድያውን ማን እንደፈጸመው ለማረጋገጥ አልቻልኩም ያለው አምንስቲ፤ ሆኖም ካነጋገራቸው የዐይን እማኞች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የሚዋጉት የህወሓት ታማኝ ኃይሎች ጥቃቱን ፈፅሟል ሲሉ ክስ መናገራቸውን ገልጿል።