ወያኔ ከነጻ አውጪ ግንባርነት ወደ አጥፍቶ ጠፊ ሽብርተኛነት ሙሉ በሙሉ የተሸጋገረች ይመስላል። ከባህርዳር እና ከጎንደር አልፋ ግጭቱን ድንበር ዘለል ለማድረግና የአለማቀፍ ማህበረሰቡን በቂ ትኩረት ለማግኘት የሄደችበት መንገድ ብዙ ነገር ያመላክታል።
1ኛ/ የህውሃት መሪዎች በወንጀለኛነት ተፈርጀው በምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው መገፈፉ ይሄ ጦርነት የሚጠናቀቀው እንድም እነሱ ቃሊቲ እስር ቤት ወርደው አለያም በውጊያው ተገድለው ብቻ እንደሆነ ጠንቅቀው ተረድተዋል። እንዳይሸሹ እንኳ ዙሪያቸው ታጥሯል። ስለዚህ ባላቸው አቅም ሁሉ ጠላት ወዳሉት አካል ያላቸውን ሁሉ መወርወር እና በቂ አለም አቀፍ ትኩረት ማግኘት ነው።
2ኛ/ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ስነ ልቦና እና በምን ጉዳይ እና መቼ እንደሚበረግግ ወያኔ ከአብይ አስተዳደርም ሆነ ከሻቢያ የተሻለ ተመክሮ አላት። ኢሳያስ ነገሩ ሁሉ ፊትለፊት እና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ሲላተም የኖረ፤ እንዲሁም ኤርትራን ከአለም አግልሎና በሩን ዘግቶ የኖረ ጊዜ ያለፈበት፣ ዘመኑን ያልዋጀ አንባገነን ነው። አብይ ለአለም አቀፉ በሸር የተሞላ ዲፕሎማሲ ጨቅላ ፖለቲከኛ ነው። ወያኔ ግን በአለማቀፉ ማህበረሰብ ጉያ ውስጥ ተወሽቃና እንደ ሱማሌን የመውረር አይነት ግዳጆችን እየተቀበለች ስትፈጽም፣ ጀነራሎቿ በሰላም አስከባሪነት በየአገሩ ሲዞሩ የኖሩ ስለሆኑ የአለማቀፉን ማህበረሰብ ስነ ልቦና በደንብ ያውቃሉ። ተንኮሉንም ተክነውታል።
3ኛ/ የኢትዬጵያ የዲፕሎማሲ ተቋማት እና ኤምባሲዎች አብዛኛዎቹ አቅም በሌላቸው ካድሬዎች የተሞሉ ስለሆኑ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን አስተሳሰብ ለመቀየር የሚችል እውቀቱ፣ ዝግጅትና ብቃቱም ስለሌላቸው አገሪቱን የሚጠቅም፣ የመንግስትን አቋም ለአለም በጥሩ ሁኔታ ለማስረዳት፣ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ለማድረስ ያላቸው አቅም ለዜሮ የቀረበ ነው። ብዙ ኤምባሲዎቻችን ውስጥ የተሰገሰጉት ካድሬዎች የዲፕሎማሲ ስራ እንዲሰሩ ሳይሆን ስደተኛውን ኢትዬጵያዊ አንድ ለአምስት ሊጠረንፉ የተላኩ ስለሆኑ ከዲፕሎማሲ ሥራ ይልቅ የቀበሌ ሥራ ላይ ነው ጊዜያቸውን የሚያጠፉት። የዲፕሎማሲ ክህሎቱም፣ ብቃቱም አይታይባቸውም። በወያኔ ጊዜ መቀመቅ የወረደው የኢትዬጲያ ዲፕሎማሲ ገና ስላላገገመ አሁን የመጣብንን ጥቃት የሚቋቋም አይደለም።
4ኛ/ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ስነ ልቦና ወያኔ ስለገባት የግጭቱን ባህሪ በሁለት መልኩ ለመቀየር እየሞከረች ነው። አንደኛው ሰቅጣጭ የሆኑ እና ሲቪሊያን ተኮር ጥቃቶችን በይፉ መፈጸም፣ በአለም አቀፍ ህግ ሊያስጠይቁ የሚችሉ የወንጀል አይነቶችን በይፋ ተናግሮ መፈጸም እና ጏላፊነቱንም በይፋ መውሰድ። ሁለተኛው ደግሞ ድንበር አቋርጦ ሌላ ሉዐላዊ የሆነን አገር፤ ኤርትራን መምታት። እነዚህ ሁለቱም እርምጃዎቿ የአለም ማህበረሰቡን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ከመሳብም ባለፈ በአብይ አስተዳደር በኩል ግጭቱን አጣጥሎ የሚደረገው ጦርነት የመርካቶ የሌባና ፖሊስ ማሳደድ አይነት ለማድረግ የተሞከረውን የረፈደ አቀራረብ ዱቄት ያደርገዋል። አለም ግጭቱን ሲቪል ዋር ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ቀንድ ግጭት አድርጎ እንዲወስድ ያደረገዋል።
5ኛ/ በአሜራካ የጸጥታ ቢሮ እና በFBI ስልጠና ሲወስዱ ቆይተው የለየላቸው ሽብርተኞች እና አጥፍቶ ጠፊዎች እንደሆኑት አልቃይዳ እና ሌሎች የምስራቁ አለም አሸባሪ ድርጅቶች ህውሃትም አለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል የተሰጣትን የሥልጠና ክህሎት በዚህ ፍልሚያ ላይ ማዋሏን እያሳየችን ነው። አሜሪካ የአፍሪቃ ቀንድ ላይ ከቀበረቻቸው time ticking ቦምብ ውስጥ አንዷ የሆነችው ህውሃት መፈነዳዳት መጀመሯን ስንቶች እንደተረዱት አላውቅም። ይሄ ጦርነት ለኔ የሚያሳየኝ ትግራይ የምትባልን አገር የማዋለድ ሚሽን ነው። ኢትዬጲያ ኤርትራ የምትባል አገር ለመውለድ የከፈለችውን የደም ግብር ዛሬ ደግሞ ትግራይን ለመውለድ እያማጠች፣ ደም እየፈሰሳሳት፣ እያቃሰተች፣ እየጮኸች ነው። አዋላጆቿም የናፈቁት ቀን የደረሰላቸው ይመስላል።
6ኛ/ ትላንት በቁጥር ብዙም ባይሆኑ ኤርትራ አትገነጠልም ሲሉ የነበሩ ኤርትራዊያን እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም ትግራይም አትገነጠልም የሚሉ የትግራይ ልጆች አሉ። ትላንት ኤርትራ እንድትገነጠል የታገሉ ኤርትራዊያን እንዳሉ ሁሉ፤ ዛሬ ትግራይ እንድትገነጠል የሚታገሉ የትግራይ ልጆች አሉ፣። ትላንት ሻቢያ እነ ኦነግን አሰልጥኖ ግንባር ላይ አብረውት ደርግን ይወጉ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ወያኔ ኦነግ ሽኔን ከጎኗ አሰልፋለች። ትላንት ኢትዬጵያ እኔ እያለው አትፈርስም አንድ ጥይት እስኪቀር እዋጋለሁ ይል የነበረ አገር ወዳድና ቆፍጣና ወታደር የነበረው መንግስቱ ጏይለማርያም ይመራት እንደነበር ሁሉ፤ ዛሬም እኔ እያለው ኢትዬጵያ አትፈርስም፣ ከሷ በፊት እኔ ልፍረስ የሚል ጏይማኖት የተጫነው፣ አገሩን የሚወድ ወታደር የነበረወ ዶ/ር አብይ አህመድ ይመራታል። ትላንት አገሬ አትደፈርም፣ ኢትዬጵያ አትገነጠልም፣ አጥንትና ደሜ ላንቺ ክብር ይሁን ያሉ ሚሊዮኖች ኢትዬጵያዊን ኤርትራ እንዳትገነጠል መዋደቅ ብቻ ሳይሆን ከተገነጠለች በኋላም ለማስመለስ ዳድቷቸዋል። ዛሬም ትግራይን ከወያኔ እጅ ለማስጣል ድፍን የኢትዬጵያ ልጆች ህይወታቸውን ለመስጠት ቆርጧሌ። ዋጋም እየከፈለ ነው። ትላንት ሻቢያን እና ወያኔን ለማውገዝ ደርግ በየከተማው ሌት ተቀን ዝቡን ለድጋፍ ሰልፍ እየጠራ ያሰልፍ ነበር፤ ዛሬም የብልጽግና ካድሬዎች ኮሮናውም ሳይበግራቸው በየከተማው ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
የእኔ ስጋት ታሪክ እራሱን እየደገመ እንዳይሆን ነው። ከመሰሪዋ ህውሃት ጋር የተጀመረው ፍልሚያ በጥንቃቄ ካልተያዘ በመቶሺዎች የደም ግብር ትግራይ የምትባል ሌላ የአምባገነን መፈንጫ አገር እንዳትወለድ ነው። ብዙዎች ከዛሬ ነገ የወያኔ ወንጀለኛ መሪዎች እጃቸው በካቴና የፊጥኝ ታስረው ልክ እንደ ሜቴኩ ጀነራል ክንፈ ተይዘው ሰብልዬ በተሰኘችው ሄሊኮፐተር ይመጣሉ ብለው ሰማይና ቴሌቭዥናቸው ላይ አፍጠው የትግራይን አገር የመሆን መርዶ እንዳይሰሙ እሰጋለሁ። የኢትዬጵያ ሕዝቡ ምኞት የእኔም ምኞት ስለሆነ በቅርቡ እንዲሳካ ከልቤ እመኛለሁ። ቶሎ የመሆኑን ነገር ግን እንጃ።
ለማንኛውም ኢትዬጵያ የተነጣጠረባትን እና ያንጃበበባትን ከፍተኛ የመበተን እና የእልቂት አደጋ ሊገዳደር የሚችል ጠንካራ የብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ሊኖራት ይገባል። ጦርነቱ ቶሎ እንዲቋጭ እና የሚደርሰውም የጉዳት መጠን እንዲቀንስ ተገቢውን ጥረት ማድረግ በግንባር የተሰለፈውን ጦር ከማጠናከር በላይ የህውሃትን ሸር ሊመክት የሚችል የተቀናጀ የዲኘሎማሲ፣ የእስትራቴጂ ቅየሳ እና የምክክር ማዕከል ኢትዬጵያ ሊኖራት ይገባል።
ወያኔ ከቻለች ትግራይን አገር አድርጋ ለመቀጠል ከድርድር አንስቶ ሌሎች መውጫ መንገዶችን ከመቧጠጥ አትቦዝንም፤ ካልቻለችም አጥፍቶ ጠፊ ለመሆን ቆርጣ መነሳቷን የሮኬት ጥቃቶቿ አሳይተዋል። አብረን ላለመጥፋትም ሆነ ትግራይን ላለማጣት ማሰብ እና ጥንቃቄ የተሞላው ስልት መቀየስ የግድ ይላል።
ቸር ያሰማን!