ኢሰመኮ ጋዜጣዊ መግለጫ
ሕዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም.
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበታ ልዩ ችሎት ለአራት ወራት ያህል በእስር በቆዩት በአቶ ለሚ ቤኛ እና በአቶ ዳዊት አብደታ ጉዳይ የዋስትና መብታቸውን በማረጋገጥ የሰጠውን ትክክለኛ ውሳኔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እውቅና እየሰጠ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት በተመሳሳይ መልኩ የሌሎችንም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ያቀርባል።
ኢሰመኮ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸውና የዋስትና ሁኔታውን አሟልተው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ሰዎች በእስር እንዲቆዩ መደረጉ ፍትሕን የሚያጓድልና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ተግባር መሆኑን በመግለጽ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸዉ በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ ማሳሰቡ ይታወሳል።
በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ስለሚገኙ ሰዎች ሁኔታ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች በማሳወቅ ክትትሉን የቀጠለ ሲሆን፤ በተለያዩ ቦታዎች አበረታች አርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም አሁንም ድረስ በተለይ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው በእስር የሚገኙ ሰዎች አሉ። ከነዚህ መካከል የአቶ ልደቱ አያሌው እና የዶ/ር ሁሴን ከድር ጉዳይ አፋጣኝ እልባት የሚሻ መሆኑን ኮሚሽኑ ያሳስባል።
ከሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ በእስር ላይ ለሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፤ አሁንም በድጋሚ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወቃል። በኢሰመኮ ምርመራ መሰረት በአቶ ልደቱ ላይ የቀረቡት ክሶች የዋስትና መብት የማያስከለክሉ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ኢሰመኮ የተመለከተው የጤንነታቸው ሁኔታ ማስረጃዎች የዋስትና መብት ጥያቄውን በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግን አስፈላጊነት ያስረዳል። ስለሆነም የአቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና መብት በአስቸኳይ ሊፈቀድ የሚገባ ነው።
በሌላ በኩል ከሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሁሴን ከድር የአጋርፋ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የዋስትና መብት ፈቅዶላቸዉ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ከመስጠቱም በተጨማሪ፣ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከፖሊስ በቀረበለት የተጠርጣሪው የምርመራ መዝገብ ላይ በሰጠው ውሳኔ ክስ ለማቅረብ የሚያበቃ ማስረጃ አለማግኘቱን ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን ዘግቷል። ይሁንና ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ ፖሊስ ለኮሚሽኑ እንዳሳወቀው በተጨማሪ ወንጀል በመጠርጠራቸው አሁንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሁሴን ከድር አብዛኛውን የእስር ጊዜ የቆዩት በአጋርፋ እስር ቤት ሲሆን፤ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተወስደው አሁንም በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ኢሰመኮ የተረዳ ቢሆንም፣ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ወዲህ ከቤተሰቦቻቸው አለመገናኘታቸው ኮሚሽኑን አሳስቦታል። ስለሆነም ዶ/ር ሁሴን ከድር በአስቸኳይ በቤተሰባቸው ሊጎበኙ የሚገባ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ሊያስከስስ የሚችል አሳማኝ ክስ ካለ በአፋጣኝ ሊቀርብ፣ አሊያም ከእስር ሊለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸው በአስቸኳይ ሊከበር ይገባል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት ‹‹ የዋስትና መብት በሕገ መንግስቱና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የተረጋገጠ መሰረታዊ መብት እንደመሆኑ፣ በሕግ በግልጽ ከተመለከቱ ሁኔታዎች በስተቀር የዋስትና መብት በተቀላጠፈ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ነው። ›› አክለውም “በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቶች የተከሳሾችን የዋስትና መብት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን እየወሰኑ መሆናቸው የሚበረታታ ተግባር ነው” ብለዋል።