ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ገደማ ፖሊሶች ነን ያሉ ግለሰቦች በአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ 6 ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መጥተው በር እንዲከፍቱላቸው የተጠየቁ መሆኑን የተናገሩት፤ አቶ አቤል አሰፋ፤ “ማንነታችሁን ሳላረጋግጥ እና ለቤተሰቦቼ ሳላሳውቅ አልከፍትም” በማለታቸው ፖሊስ ነን ያሉት ግለሰቦች ተጨማሪ ኃይል ያስፈልገናል እያሉ ወደመጡበት እንደተመለሱ ተናግረዋል።
ሆኖም ግለሰቡ ወደ ሥራ ከሄዱ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ ከቀኑ 9 ሰዐት ሲሆን የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው እና ሽጉጥ ታጥቀው ተመልሰው በመምጣት ” አቶ አቤል ወንጀል ሠርተው ስለታሰሩ እኛ ቤታቸውን ልንበረብር ነው የመጣነው ” በሚል የተቆለፈውን በር ሰብረው በመግባት በካዝና ውስጥ ለንግድ አገልግሎት የተቀመጡ አንድ ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ ብር ግምት ያላቸውን የወርቅ ጌጣጌጦችን ሰርቀው ተሰውረዋል።
የፈጻሚዎቹን ማንነት ለማወቅ በተደረገው ክትትል ካዝናውን ጭኖ የተሰወረውን ተሽከርካሪ፣ በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉ 5 ተጠርጣሪዎችን፣ ለወንጀል ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የፖሊስ የደንብ አልባሳት፣ ሽጉጥ፣ ካቴና እና ስለቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።