ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ትናንት ሌሊት ኅዳር 10/2013 ዓ.ም ከእኩለ ሌሊት በኋላ በባህር ዳር ከተማ ሌሊት 7 ሰዐት ከ30 ገደማ ላይ የሮኬት ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ አየር ኃይል እርምጃ እንደሚወስድ አሰታወቀ።
እስካሁን ከህወሓት በኩል በተተኮሰው ሮኬት የደረሰው ጉዳት መጠን ባይታወቅም፤ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን በበኩሉ በሰዎች ላይ የደረሰ ምንመ ጉዳት የለም ብሏል።
የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ሌሊት 7 ሰዐት ከ40 ላይ በባሕር ዳር የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ፣ ጥቃቱን ያደረሰው ህወሓት ነው ሲል በይፋ ወንጅሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ ፤ “የመጨረሻ ሞት ስለሆነ ወደ ሕዝብ ነው የተኮሱት፣ ግን የደረሰ ምንም ጉዳት የለም፤ ጫካ ላይ ነው የወደቀው። እዚያ አካባቢም ሰው አልነበረም” ሲሉ ሂደቱን አስታውሰው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ አፀፋዊ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ለሸገር ራዲዮ ተናግረዋል።