ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ የሰየሟቸው ልዑካን መፍትኄ ለማፈላለግ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ቢነገርም ፈጽሞ ድርድር እንደማይኖር የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።
ሲሪል ራማፎሳ ሦስት ታዋቂ አፍሪካዉያንን በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ግጭት ዙሪያ እንዲያሸማግሉ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ አድርገው እንደሰየሙ በትዊተር ገጻቸው ላይ ቢያሰፍሩም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የልዑካን ቡድኑን ተቀብለው ከማናገር ውጪ ወደ ድርድር እንደማይገቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ህወሓትን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር አሸማግላለሁ የሚሉት ፕሬዝዳንት ራማፎሳ፤ ጉዳዮን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለተጓዙት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹላቸውና መልዕክተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ግጭቱ መፍትኄ በሚያገኝበት መንገድ ላይ ድጋፍ ያደርጋሉ የሚል መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።
ወደ ኢትዮጵያ የተለኩትና የተመረጡት ልዩ መልዕክተኞቹ የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖ፣ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰንና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት ጋሌማ ሞትላንቴ መሆናቸውም ታውቋል።