የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም በቅርቡ ሠሜን እዝ ይባል ስለነበረው ግብረ-ኃይል መግለጫ አቅርበዋል።
መግለጫው፣- እዙ የነበረውን ወታደራዊ ኃይልና የማድረግ ችሎታ መገመት የሚያስችል ነበር። የክፍለ ጦሮችን ብዛት ከነመለያ ቁጥራቸውና ዓይነታቸው አቅርበውልናል፤ እስከዛሬ ይህ በይፋ አይታወቅም ቢያንስ እኔ አላውቅም ነበር። ዝርዝሩ እንዲህ ነው፡ –
ሜከናይዝድክ/ጦር – 4ኛ፣ 5ኛ፣ 7ኛ፣እና 8ኛ ፣ እና እግረኛ/ክ/ጦር – 11ኛ፣ 20ኛ፣ 23ኛ፣እና 31ኛ ።
ሜከናይዝድ ይሁን እግረኛ፣በአንድ እዝ ስር ያለ 8 ክፍለ ጦር፣በጣም ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል ነው።
በግርድፉም ቢሆን ገባ ብለን እንየው፦ ሜከናይዝድና እግረኛ ክፍለጦር ልዩነት ስላላቸው፣ ነገሮችን ቀለል ለማድረግ፣ ሁሉንም በአንድ መደበኛ እግረኛ ክፍለጦር ሚዛን እንመልከታቸው።
የሰው ኃይል፣- አንድ ክፍለጦር በተለያየ ምክንያት፣ ከ7000 እስከ 11000 በሚደርስ የሰው ኃይል ሊደራጅ ስለሚችል ዝቅተኛ-መካከለኛ የሚባለውን 8000 ወስደን ብናሠላው፣8ክ/ጦር x 8000 = 64,000 የሰው ኃይል ይሆናል።
ከባድ መሣርያ-ታንክ-መድፍና ቢ ኤም ፡ -በተለመደው አሠራር፣ በአቋም፣አንድ መደበኛ እግረኛ ክፍለጦር አንድ የታንክ ሻለቃና አንድ የመድፍ ሻለቃ ይኖረዋል። አንድ የታንክ ሻለቃ በትንሹ 21 ታንኮች፣ አንድ የመድፍ ሻለቃ ደግሞ እንዲሁ 25 መድፎች ይኖረዋል።
በዚያ ሂሳብ፣ የሠሜን እዝ 8 ክፍለ ጦሮች 8 x 21 = 168 ታንኮች፣ 8 x 25 = 200 መድፎች፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍለጦር አንድ ሻለቃ ባለ 12 ቢ ኤም ማለትም 8 x 12 = 96 ቢ ኤም አለው/ነበረው ማለት ነው።
ከነኝህም ሌላ፣ በርካታ ወታደራዊ የውጊያ መሣርያዎችን፣ እነ በ.አም.ፐ.ን፣ ሺልካን. ዙ-23 ንና ሌሎችም የውጊያና የውጊያ መርጃ መሣርያዎች መኖራቸውን ሳንዘነጋ ነው።
የሠሜን እዝ ሲባል ይህ ብቻ እንዳልነበረም ይታወቃል። የመቀሌ የአየር ኃይል አየር ምድብና፣ የርሱ አካል የሆነው፣የአየር መከላከያ Air Defense Missile Regiment ቢያንስ ለዘመቻ በእዙ ስር ስለ ነበሩ የነሱም ጉዳይ አለ። የክልሉን አየር ክልል ለበረራ መዝጋት/አደግኛ ማድረግ የሚያስችለው ነው። ለጊዜው ፓይለት ባይገደውም ተዋጊ አይሮፕላን ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም።
ከኤርትራ ጋር በነበረው የጦርነት ሁኔታ ምክንያት፣ያለ ተጨማሪ እደላ እዙን ለረዥም ጊዜ ሊያዋጋው የሚያስችለው ስትራተጂክ ረዘርቭ ማለትም፣ የነዳጅ፣ የጥይት፣ፈንጂ፣ ለመድፍና ለተዋጊ ኤሮፕላኖች የሚያስፈልግ የቦምብና ሮኬት፤ ሌሎችም የሎጂስቲክስ ክምችት ተደራጅቶለት ነበር። አሁንም በጁ ነው።
ህዳር 4 ቀን ምሽት ባህር ዳርና ጎንደር ኤየር ፖርቶች ላይ ባደረሰው ጉዳት፣ ወያኔ በትንሹ፣ ከ 500 ኪሎ ሜትር በላይ መወንጨፍ የሚችል surface to surface (guided?) missile እንዳለው አረጋግጧል።
እንግዲህ፣ ጥቃት ደረሰበት የተባለው የሠሜን እዝ ይህ ግዙፍ ኃይል መሆኑ ነው። ዶ/ር አቢይ በደፈናው “ጥቃት ደረሰበት” ዶ/ር ደብረፅዮንም “እጅ ወደ-ላይ! ብለን መሣርያውን ገፈፍን” ያሉት፣ ሁለቱም የሚያስኬድ አይመስልም። «ጥቃት የፈፀመው እዙ ራሱ በራሱ ላይ ነው» ቢባል የተሻለ ነው።
በሠሜን እዝ ውስጥ የ “ብሄር ተዋፅዖ መመጣጠን” የሚባለው ሥራ ባለ መሠራቱ የእዙ ሠራዊት 85% ከአመራር እስከ ተራ ተዋጊ የትግራይ ተወላጅ ሆኖ ኖሯል። ቀሪው 15% ወይንም 9600-10,000 ያህሉ ብቻ ትግራዋይ ያልሆኑ «በወል ስማቸው» ውድ የኢትዮጵያ ጀግና ልጆች ነበሩ።
ወያኔ መብረቃዊ ዘመቻ /blitz (Krieg) operation/ ባለው ‘ብልጭታዊ’ ኦፐሬሽን የመታው ይህን አሥራ አምስት በመቶ፣ ኢትዮጵያዊ የእዙን አካል ለብቻ ነጥሎ ነው። የመታው ደግሞ በእዙ ውስጥ ሲያደባ የቆየው የአሁኑ የ “ትግራይ ሠራዊት” የሆነው ኃይል ነው።
ወደ ኋላ ሄዶ ነገር መቀስቀስ አይሁን እንጂ፣ በመስከረም ወር 2011 ዓ ም መጀመርያ ላይ፣ ዶ/ር አቢይ የተወሰነ የሠሜን እዝ ጦር ክፍሎች ከክልሉ ውጪ ወደ ሌላ የግዳጅ ቀጣና እንዲነቃነቁ ትዛዝ ሲሰጡት፣ «በውሪና ህዝብ-ተሰብስቦ-መንገድ-ዘጋብኝ» አሳቦ አሻፈረኝ ሲል ችላ የተባለው አሁን ብቅ ያለው አፈንጋጭ ኃይል እንደነበር ያኔም አሁንም ግልፅ ነው።
«የዘብ ተረኛነቴን፣ የተካኝ ጓዴ፣ ወገኔ፣ ይጠብቀኛል» ብሎ ባሸለበው ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ላይ ጥቃት ይባል ፍጅቱን የፈፀመው ይህ ያፈነገጠ የእዙ አካል፣እጄን ቤጄ እንደሚባለው ሆኖ እንጂ፣ ከውጪ የመጣ ሚሊሺያ አይደለም። ሚሊሺያም፣ ልዩ ኃይልም ትግራይ ውስጥ የነበረ ሌላም ኃይል ተባብሮ፣ ፈቅዶ ካልሆነ በቀር፣ ያንን ግዙፍ የሠሜኑን ‹እዝ እጅ ወደ ላይ› ሊያስደርግ የሚችል ኃይል አልነበረም።
እና በዚህ ሁኔታ በተፈፀመው ክህደት ከአስር ሺዎቹ ስንቱን የኢትዮጵያ ውድ የሠራዊቱ አባላት እንደፈጀ ቁጥሩ አይታወቅ ይሆናል እንጂ፣ በመለዮ ለባሹ ላይ የተፈፀመ የዘር ፍጅት መሆኑ ጥርጥር የለውም።
ግልፅ መሆን ያለበት ትልቁ ጉዳይ ታድያ፣ የዚህ 15% በመቶ የሰው ኃይል መወገድ፣የእዙን ‹ወታደራዊ የማድረግ ችሎታ› የሚቀንስበት ማደናገርያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ቅንጣት አይቀንስበትም።ያንን የጎደለ ኃይል፣ በቀናት ውስጥ ከትግራይ ልዩ ኃይል ማሟላት ይችላል። ምናልባትም ወያኔ አሠልጥኖ ጠብቆም ይሆናል።
ዓላማው እዙን በዘር ንጥር ያለ ለወያኔ ታዛዥ የሆነ «ወርቃማ የትግራዋይ ሠራዊት» መፍጠር ስለነበር፣ በዚህ ረገድ በእጅጉ ተሣክሎታል ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያን የሠሜን እዝ እንዳለ ከነ ሙሉ ትጥቁና ድርጅቱ “የትግራይ ሠራዊት” አድርጎታል።
ከላይ የቀረበው የ እዙ ኃይል ስሌት የተጋነነ ነው በ 25% ይቀነስ ቢባል እንኳ አሁንም የምንነጋገረው 48,000 የሰው ኃይል፣126 ታንክ፣150 መድፍና 72 ቢ ኤም-21 የታጠቀ ስለሚሆን ቀላል ኃይል አይደለም።
እንግዲህ፣ ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምን፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ኃይል ጋር አደገኛና ውጤቱም አስከፊ ሊሆን ወደሚችል ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች።
ይህንን ለማስወገድ የሚዘጋጅ ወታደራዊ ዕቅድ፣ በቀላሉ የማይበገር ከሚያስፈልገው በላይ የታጠቀ ወታደራዊ ኃይል መሆኑን ብቻ ሣይሆን፣ በዘር የተደራጀ፣ አጥፍቶ የመጥፋት ዓላማ ያለው ክፉ ባላጋራ መሆኑን ያገናዘበ መሆን አለበት።
ይህ ኃይል በጦርነት የተፈተነ ኃይል መሆኑን፣ ጠንካራና ልምድ ያላቸው ወታደራዊ መሪዎችና ተዋጊዎች ያሉት መሆኑን ታምኖ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት።
እቅዱ «መሐል አገሩ ሊፈጅህ እየመጣ ነው» የተባለ ያገረገረ የትግራይ ህዝብ ከጀርባው ያለው መሆኑንም የተገነዘበ መሆን አለበት። የፀረ-አማራ ቅስቀሳ ለትግራይ ህዝብ ሱፐር-ግሉ ሆኖ ወያኔን ለምኒልክ ቤተ መንግሥት እንዳበቃ ማስታወስ ይበጃል።
በአገሪቱ ውስጥ ያሠለፈው በርካታ የአምስተኛ ረድፍ ሠራዊቱንም መዘንጋት አይገባም። ወያኔ በሚሠጣቸው ፕሮግራም አደጋ ሊያደርሱ ስለሚችሉ ታሳቢ መሆን ያለባቸው ናቸው። የሠራዊቱን ኃይል ለመበታተን የተዘጋጀ ስውር ኢጁ መሆኑን ተገንዝቦ የእቅዱ አካል ማድረግ ያስፈልጋል። የመከላከያው ፀረ-መረጃ ክፍል ተጠናክሮ ሠራዊቱን ከወያኔ ሠርጎገቦች ነቅቶ መጠበቅ አለበት።
ጠላትን የናቀ ይዋረዳል። የዚህን ወንበዴ ኃይል ዝቅ አድርጎ መገመት ትርፉ ውርደትና አገርንና ህዝብን ለአደጋ መጋበዝ ይሆናል። የሚስተዋለው በእርግማን የታጀበ ማቃለልና ማናናቅ በጣም አደገኛ ነው። በሽለላና ቀረርቶ የጠፋና የሚጠፋ ጠላት የለም። እርግማንም አይረዳም። ሰንበሌጥም «በንፋሱ እንጂ መች በእርግማኑ” ብላለችና።
ገና ዋናው ፍልሚያ ሣይጀመር በትንንሽ መቆራቆዞች የተገኙ ውጤቶች ገዝፈው በቃለ አጋኖ ሲነገሩ ይሠማል። ድል አይነገር አይባልም፣ ግን ሚዛን ይጠበቅ። ከጠላት በኩል የሚወረወረው ቦምብና ጥይት እንጂ አበባና ሎሚ ስላይደለ ጉዳት ይኖራልና።
ከሠላማዊ መፍትሄ ይልቅ ጦርነት እንዲህ የግዴታ ምርጫ መሆኑ እጅግ በጣም ያሳዝናል። ክፉ ምርጫ ነው። «የግዴታ ምርጫ» መሆኑ ካልቀረ ዘንዳ፣ በወታደራዊ ዕውቀት፣ ብልሃት፣ ጥንቃቄና ልክ በሌለው ትዕግስት መመራቱ አማራጭ የለውም።
አበቃ።
|| ከአብዮታዊው ሰራዊት ገፅ ||