“ሳምሪ” የተሰኘ ቡድን ከትግራይ ሚሊሻ ጋር በመተባበር በማይካድራ ከ600 በላይ ሰዎች መግደሉን...

“ሳምሪ” የተሰኘ ቡድን ከትግራይ ሚሊሻ ጋር በመተባበር በማይካድራ ከ600 በላይ ሰዎች መግደሉን ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አጋለጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ህወሓት በማይካድራ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ቢያንስ 600 ሰዎች አሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉና ቀጠሩ ከዚህ እንደሚበልጥ ዋነኛ ምስክሮችን በማነጋገር የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው የማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት በአካባቢው የነበረው የትግራይ ሚሊሻና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር  “ሳምሪ” ከተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን ጋር በመተባበር መፈጸሙን የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አጋልጧል።
በተለይ ‹‹አማሮችና ወልቃይቴዎች›› ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል ያለው ኢሰመኮ እስከ አሁን ባገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ እጅግ ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል›› ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፤ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY