ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በማይካድራ ላይ የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ በማንነት ላይ ያነጣጠረና በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ታጣቂዎች የተፈጸመ ከባድ ወንጀል መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አስታወቁ።
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች፣ የሆስፒታል ሰራተኞች እና ሌሎችንም አካላትን በማነጋገር መረጃ ማጣራቱን የተናገሩት ዶክተር ዳንኤል፤ የህወሓት ጁንታው ቡድን በማይካድራ የፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት በአይነቱ ለየት ያለ ከባድ የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንደሆነም ገልጸዋል።
መርማሪ ቡድኑ በደረሰበት እና ባገኘው መረጃ መሠረት ጥቃቱ የተፈጸመው ብሔርን መሰረት ባደረገ መልኩ መታወቂያ እያዩ በመለየት በዘግናኝ ጭፍጨፋ እንደሆነም በኮሚሽነሩ ይፋ ተደርጓል።
ህወሓት ባሰማራው ጨፍጫፊ ቡድን ይህ ዘግናኝ ድርጊት መፈጸሙ እና የአካባቢው የህወሓት ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች በየደረጃው ድርጊቱን ይፈጽሙ እና ያስፈጽሙ እንደነበር ያጋለጡት ዶክተር ዳንኤል በቀለ፤ እነዚህ አካላት በፍጥነች በህግ ተጠያቂ እንዲደረጉም አሳስበዋል።