ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የመከላከያ ሠራዊቱ መቀለ ከተማን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ተከትሎ አራተኛውና የመጨረሻው ነው የተባለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሙስ ዕለት ሠራዊቱ የመጨረሻው ምዕራፍ ያሉትን ሕግ የማስከበር ዘመቻ እንዲያካሂድ ካዘዙ በኋላ ቅዳሜ ኅዳር 19/2013 ዓ.ም የክልሉን ዋና ከተማ የፌደራል ሠራዊቱ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩ ተረጋግጧል።
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ በመቀለ በከተማ ነዋሪ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ በተካሄደ ዘመቻ ሠራዊቱ ቅዳሜ ከሰዐት በኋላ መቀሌን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል ሲሉ ገልጸዋል።
የፌደራል ፖሊስ በሕግ የሚፈለጉ የህወሓት አባላትን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ እንደሚያከናውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀጣይ ትኩረታችንም ክልሉን መልሶ መገንባትና ሰብኣዊ ድጋፎችን ማድረስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሠራዊቱ መቀሌን በተቆጣጠረበት ጊዜ የግጭቱ መነሻ ነው የተባለውና በህወሓት ኃይሎች ጥቃት እንደተፈጸመበት የተነገረውን የሰሜን ዕዝ ካምፕን መያዙን፣ እንዲሁም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ በሺኅ የሚቆጠሩ የዕዙ አባላትን አስለቅቋል።
የሰላማዊ ሰዎች ደኅንንትን በጠበቀ ሁኔታ ወደ መቀሌ የገባው የፌደራል ሠራዊት የከተማዋን አየር ማረፊያና የክልሉን አስተዳደር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ቁልፍ ሕዝባዊና ሌሎች ተቋማትን በዋናነት መቆጣጠሩን መንግሥት ይፋ አድርጓል።