ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ተጠርጥረው ሒሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገው ደንበኞች ውጪ፣ በትግራይ ክልል በሚገኙ ባንኮች ሒሳብ የከፈቱ እና ከትግራይ ውጭ ያሉ ደንበኞች በያሉበት አካባቢ ሒሳባቸውን ከዛሬ ጀምሮ ማንቀሳቀስ ይችላሉ ተባለ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወጣው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል እየተከናወነ ባለው የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የፀጥታው ሁኔታ ለባንኮች አመቺ በሆነባቸው ከተሞች ባንኮች ተከፍተው ሥራ እንዲጀምሩ ከሚመለከታቸው ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል።
የፀጥታው ሁኔታ አመቺ ባልሆነባቸው ከተሞች አሁንም ባንኮች ተዘግተው የሚቆዩ መሆኑን ያረጋገጠው ብሔራዊ ባንክ፤ በትግራይ እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ ምክንያት የፀጥታው እና የኔትዎርክ ሁኔታ እስኪሻሻል ባንኮች ተዘግተው እንዲቆዩ ተወስኗል ብሏል።