ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስር ላይ የሚገኙትና ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች ዳግም ለታህሳስ 13 ተቀጠሩ።
በእነ እስክንድር የክስ መዝገብ የተከሰሱት 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን ዐቃቢ ሕግ ማቀረብ ባለመቻሉ ክሳቸው እንዲቋረጥ ዛሬ የተሰየመው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል።
በአንጻሩ የሽብርተኝነት ክስ የተመሠረተባቸው የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች እስክንድር ነጋ ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዮም እና አስካለ ደምሌ ደግሞ ከ15 ቀን በኋላ ታህሳስ 13 ቀን ዳግም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
ከላይ የተጠቀሱት አራት የፓርቲው አመራሮች የተፋጠነ ፍትህ እንዲሰጣቸው ከጥቂት ቀናት በፊት የጻፉትን ደብዳቤ ጨምሮ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ፍ/ቤቱ ዛሬም በድጋሚ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የእነእስክንድርን ችሎት ለመዘገብ የተገኙ የተለያዮ ሚዲያ ባልደረቦች “ቦታ ሞልቷል” በሚል ሀሰተኛ ምክንያት እንዳይገቡ የተደረገ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ችሎቱን ለመታደም ከመጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች መካከልም የአፄ ምንሊክ፣ የአፄ ቴዎድሮስና የእስክንድር ነጋ ምስል የታተመባቸው የተለያዮ ቲሸርት የለበሱ ወጣቶችም በፀጥታ ኃይሎች ከመሀል እየተነጠሉ ተሰብስበው ከፍርድ ቤቱ ግቢ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል።