ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስር ላይ የነበሩት ልደቱ አያሌው በ30 ሺኅ ብር ዋስትና ከእስር ተፈተው ጉዳያቸውን ከውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ተወሰነ።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምሥራቅ ችሎት መወሰኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለዋስትና የተጠየቀውን ገንዘብ ሲፒኦ እያሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ “ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ” በሚል የቀረበባቸው ክስ እንዲሻሻል ባዘዘው መሠረት ዐቃቤ ሕግ የተሻሻለውን ክስ ለፍርድ ቤት አቅርቦ ነበር። ይሁን እንጂ በቀረበው ክስ ላይ ጠበቆቻቸው መቃወሚያ አሰምተው፤ ደንበኛቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን በጠየቁት መሠረት፤ አቶ ልደቱ በ30 ሺኅ ብር ዋስትና ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን በውጪ እንዲከታተሉ ወስኗል።
በዚህም መሰረት አቶ ልደቱ ከእስር ተፈተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን ለማወቅ ተችሏል።