የእኛን ሞት ሲሞቱ፣ የእነሱን ህይወት እንኑር! || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

የእኛን ሞት ሲሞቱ፣ የእነሱን ህይወት እንኑር! || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

ሰሞኑን ስለመከላከያ ሰራዊታችን አስባለሁ፡፡ የሰሜን እዝ ጓደኞቻቸውን በተኙበት ገድለው፣ ለአረመኔ ጥማታቸው ሬሳቸውን ጭምር ያሰቃዩትን ሳስብ፣ የወታደሮቹ ስብእና ከአንድ ጨካኝ ሽፍታ የባሰ እንደነበር አስብና ይህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት እንደገና በአዲስ መልክ ለማደራጀት የተሰጠ እድል አድርጌው እጽናናለሁ፡፡.

እኔ በብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ተሳትፌ፣ ለሁለት አመታት ተኩል የመከላከያ ሰራዊቱ አባል በመሆኔ እኮራለሁ፡፡ ያ ሰራዊት እንኳን በጦር ሜዳ በሰላም ወረዳ የወገኑን ሞት የሚሞት ሰራዊት ነበር፡፡ የእኔንና የበርካታ ብሄራዊ ወታደሮችን ሞት የሞተው ምክትል መቶ አለቃ ላቀው በዛብህ የዚያ ሰራዊት አባል ነበር፡፡ እሱ የበርካቶቻችንን ሞት ሞተ፤ ስንቶታችንን የእሱን ህይወት አርአያ አድርገን ለሀገርና ለወገን እንደምንኖር አላውቅም፡፡ . . . እነሆ ከ‹‹የማይጻፍ ገድል›› ውስጥ የተቀነጨበ የም/መ/አለቃ ላቀው በዛብህ የመስዋእትነት ታሪክ፡፡

በነገራችን ላይ የዚህ ጀግና ባለቤት በህይወት አለች፡፡ እሱ ሲሞት ልጃቸውን ነፍሰ ጡር ነበረች፡፡ የጀግናው ልጅ በማደጎ ሄዶ ፈረንሳይ ሀገር ይኖራል፡፡

ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን፣ 1976 ዓ.ም፣ ከጠዋቱ ልክ በሶስት ሰዓት፡፡
‹‹አሁን ቦንቡ ለአጠቃቀም ዝግጁ ሆነ ማለት ነው›› አለ የም/መ/አለቃ በቀኝ እጁ የያዘውን ቦንብ ለግራው እያቀበለ፡፡ አፈገፈግን፡፡ መፍራታችንን አውቋል፡፡ ፈገግ አለ፡፡ ቦንቡን በግራ እጁ እንደዋዛ እንደያዘ፣ ‹‹በቃ አለቀ፤ . .. አሁን ለስራ ተዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን ሁለት ሽቦዎች ቀና ካደረጋችሁ በኋላ፣›› ቀለበቱን በብብታቸው ቆልፈው ይዘው ቁልቁል ታጥፈው የነበሩትን ሁለት ሽቦዎች አቃናቸው፡፡ ‹‹ . . ጣታችሁን እዚህች ቀለበት ውስጥ አስገብታች …›› የቀኝ እጁን የሌባ ጣት ቀለበቱ ውስጥ አስገባው፤ ‹‹ከዚያ ቀለበቱን መሳብ ነው፡፡›› በቀኝ እጁ የመሳብ … የመመንጨቅ ሁኔታ አሳየ፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን ጣቱ ሙሉ በሙሉ ከቀለበቱ አልወጣም ነበር፡፡ ቀለበቱን መነጨቀው፡፡ ይህን ስላልጠበቀ የመጠበቂያ ቅጠሉን ከቦንቡ ጋር አልጨቆነውም ነበር፡፡
‹‹ዞር በሉ! ዞር በሉ!›› በግራ እጁ ቀለበቱ የተነቀለለትን ቦንብ እንደያዘ፣ በግራ እጁ እንድንሸሽ ምልክት እያሳየን፣ በከፍተኛ ድምጽ ጮኸ፡፡ ከእኔ በስተቀር ያመነው ያለ አይመስለኝም፡፡ የጅምላ ሳቅ! ያ ፈገግታ የተረጨበት፣ ፊቱ ከመቅጽበት አመድ መስሎ፣ ገርጥቶ ተመለከትኩት፡፡ ከፊት ቆሜ ስለነበር ጭንቀቱ በግልጽ ታይቶኛል፡፡ ወደኋላ ሁለቴ ተራመድኩ፤ ከፊተኛው ረድፍ መጥቼ ሁለተኛው ረድፍ ገባሁ፡፡ የትምጌታ ቦታዬን ተሻምቶ ወሰደ፡፡

‹‹እባካችሁ ዞር በሉ! . . . ባላችሁበት ተኙ!›› እየጮኸ ምልምሎች እንደጉንዳን የሚርመሰመሱበትን ሜዳ ቃኘ፤ ስንት ሞት በእጁ እንደጨበጠ ከእርሱ በቀር የሚያውቅ የለም፡፡በመዳፉ ውስጥ የጨበጣቸውን ሞቶች፣ በዚህ ሁኔታ ሊያቆያቸው የሚችለው ለሰኮንዶች እድሜ ብቻ ነው፤ ደቂቃ አይሞላም፡፡ . . . ከዚያ ከመዳፉ ይወጣሉ፡፡. . . ይረጫሉ፡፡
‹ወዴት ይወረውረው ይሆን?›
ጦር ሜዳ ቢሆን ወዴት እንደሚወረውረው ያውቃል፡፡ ሳንጃውን ወድሮ ወደ ምሽጉ የሚንደረደረውን ጠላት ያጨስበት፣ ይጠብስበት ነበር፡፡ እዚህ ያለው … ሜዳውን የሞላው ጠላት አይደለም፡፡ ገና ብዙ ተስፋ የሰነቁ ምልምሎች ናቸው፡፡ ግን ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡

ባለሁበት ቁጢጥ አልኩ፡፡ የትምጌታና ሌሎቹ በፊተኛው ረድፍ ያሉ ምልምሎች እንደቆሙ ናቸው፡፡ በአሰልጣኙ ‹ቀልድ› አለመበርገጋቸውን፣ አለመፍራታቸውን፣ ያለመስዋዕትነት፣ ለቀልድ ባለመበርገግ ብቻ ጀግና መሆናቸውን ለማሳየት የፈለጉ ይመስላሉ፡፡ የተወሰኑት ግን በም/መ/አለቃው ተደጋጋሚ ጩኸት ግራ ተጋብተው፣ ለመሸሽ፣ ለመቀመጥ፣ ለመተኛት እየሞከሩ ነው፤ ቢዘገይም፡፡ ቀለበቱን ባወለቀ ቦንብ ፊት ጊዜ የሚለካው በሰከንድ ሽርፍራፊ ነው፡፡ ለሰኮንድ መዘግየት ወይም መፍጠን የአንድን ሰው እጣ የህይወትና ሞት ያህል ያራርቀዋል፡፡

ም/መ/አለቃ ላቀው በዛብህ ቦንቡን እንደጨበጠ ለሶስተኛ ጊዜ፣ ‹‹ዞር በሉ! ባላችሁበት ተኙ!›› አለና ጮኸ፡፡ ጩኸቱ ተስፋ መቁረጥም የተቀላቀለበት ነበር፡፡ የሚናገረው ለእኛ … አጠገቡ ላለነው ይሁን እንጂ፣ አሻግሮ የሚመለከተው በሜዳው ላይ እንደአሸን የፈሰሱትን ምልምሎች ነው፡፡

‹በየትኛው አቅጣጫ ሊወረውረው፣ እነማን ላይ ሞት ሊፈረድ ይሆን? መቼም መወርወሩ አይቀርም! ይወረውረዋል፡፡ ከዚያ፣ ድብልቅልቅ ያለ የፍንዳታ ድምጽ! በዚያ ላይ የጫካው ገደል ማሚቱ ተቀባብሎ ሙሾ ይደረድርበታል፡፡ ከዚያ የገደል ማሚቶው ሙሾውን ሲያቆም፣ አዋራውና ጭሱ ሲረጋ፣ የሞተ… የቆሰለ… ምልምል ይቆጠራል፡፡ አርቆ ስለሚወረውርም እኔን አያገኘኝም፡፡› በዚያች ቅጽበት አዘውትሬ እንደማደርገው ለሽንት ወደ ሜዳው ዳርቻ፣ ወይም ወደ ጫካው አለመሄዴን እንደ ጀግንነት ቆጠርኩት፡፡

ም/መ/አለቃ ላቀው ‹‹ከአንድ አብዮታዊ መኮንን በማይጠበቅ እንዝህላልነት ምልምሎችን የገደለና ያቆሰለ፣ ፀረ አብዮት . . ›› ተብሎ ሞት ሲፈረድበት … በሴኮንድ ውስጥ ከሚፈራረቅብኝ ሀሳብ ጋር እየታገልኩ በደረቴ መሬት ተኛሁና ቀና ብዬ ተመለከትኩ፡፡
ም/መ/አ/ላቀው ፊቱን አዞረ፡፡ ጀርባውን ሰጠን፡፡ ‹ከጀርባው ካለው ዋርካ አሻግሮ ሊወረውረው ነው፡፡› በዚያች ቅጽበት ዙሪያውን ቃኝቶ ይህን መወሰኑ ታላቅ ወታደርነቱን አሳየኝ፡፡ ብዙዎቹ ምልምሎች ቁልቁል ወደ ተዳፋቱ ነው የተበተኑት፤ ከዋርካው ጀርባ ያሉት ምልምሎች ከአምስትና ከስድስት አይበልጡም፡፡ ወደዚያ ከወረወረው፣ ግፋ ቢል የሁለትና የሶስት ምልምል ህይወት ቢጠፋ ነው፡፡

‹እንዴ!› ም/መ/አለቃ ላቀው፣ ቦንብ የያዘውን እጁን ከአናቱ በላይ አንስቶ ቦንቡን አልወረወረውም፡፡ በሁለት መዳፎቹ ጭብጥ አድርጎ ይዞ ሆዱ ላይ አጣበቀው፡፡
‹እንዴ! ምን ሊያደርግ ነው!?›
በርከክ አለ፡፡ የእናት ሞት እንዳንገበገበው ለቀስተኛ፣ በሁለት እጆች ቦንቡን እንደጨበጠ፣ ተንበርክኮ፣ ከወገቡ ጎንበስ… ጭብጥ … ኩርምት…
‹‹ዷዷዷዋዋዋ … ›› ታላቅ የፍንዳታ ድምፅ አካባቢውን አናወጠው፡፡ ከዋርካው ላይ አእዋፍ ወደ ሰማይ በረሩ፤ ቅጠሎች ወደ መሬት ረገፉ፡፡ ጫካው የቦንቡን ድምፅ እየተቀባበለ አላቀሰው፤ የም/መ/አለቃውን መስዋእትነት ዘፈነው፡፡ ከአፍታ በኋላ ጭንቅላቴን ከቀበርኩበት ቀና አደረኩ፡፡ የቆሙት ምልምሎች በያቅጣጫው ሮጠዋል፡፡ ተነሳሁ፡፡ ሁላችንም በዝግታ ወደ ም/መ/አለቃ ላቀው በዛብህ ተጠጋን፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ተንበርክኮ፣ ተጨብጦ በነበረበት ቦታ ላይ ምንም ነገር የለም፡፡ በስተግራ አንድ ሁለት ሜትር ያህል ርቆ ለብሶት የነበረው ቱታ ተተልትሎ፣ በደም ተጨማልቆ ወድቋል፡፡ ‹በየአንዳንዱ የቦንቡ ፍንጣሪ የተቦጫጨቀው ሰውነቱ ሜዳውን ሞልቶታል› ከማለት በቀር ዝርዝር ሁኔታውን መግለጽ ይሰቀጥጣል፤ ያውም ሊገልጸው የሚችል ቋንቋ ከተገኘ፡፡ በዙሪያው ከነበርነው ምልምሎች ውስጥ አንድም የቆሰለ እንኳን የለም፡፡ የሁላችንንም ሞት እሱ ሞቷል፤ እንደ እየሱስ!

LEAVE A REPLY