ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን በመቐለ ከተማ ልዩ ስሙ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለጦርነት ዓላማ ሊያውለው በድብቅ ቀብሮት የነበረ 13 የነዳጅ ታንከር መገኘቱ ተነገረ።
በታንከሩ ውስጥ ከ200 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ መገኘቱ ተረጋግጧል። በመከላከያ ሠራዊት የ25ኛ ፈንቅል ክፍለ ጦር 2ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ ምክትል ኦፕሬሽናል አዛዥ ሻምበል ዮሐንስ ማቲዎስ፤ ይህ ነዳጅ ጁንታው ለጦርነት ዓላማ አስቦ በድብቅ አስቀምጦት የነበረ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከሀዲው ቡድን የትግራይ ሕዝብ በነዳጅ እጥረት እንዲቸገር በማድረግ ዘርፎ ለራሱ እኩይ አላማ ቀብሮት መቆየቱን የጠቆሙት ሓላፊው፤ ጁንታው የደበቀው ታንከር እንዲገኝ የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን አስረድተዋል።
በተያያዘ ዜና በአካባቢው ተቀብሮ ለነዳጅ ማጠራቀሚያ ሊውል የነበረ ተጨማሪ ዘጠኝ ታንከር መገኘቱንም ለማወቅ ተችሏል።