ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም የሚጠበቅባቸውን አሟልተው እንዲያቀርቡ 12 ፓርቲዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ።
የማጣራት ሂደት እየተከናወነባቸው ከሚገኙ ድርጅቶች መካከል በአቶ ማሙሸት አማረ የሚመራው የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እንደሚገኙበት ታውቋል።
በተመሳሳይ የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ፣ ነገር ግን የቴክኒክ መስፈርቶች ማሟላት ይቀራቸዋል የተባሉ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ፣ አሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይን ጨምሮ ሠባት ፓርቲዎች መኖራቸውን ቦርዱ አስታውቋል።
በምዝገባው ሂደት የሚጠበቅባቸውን ሙሉ ለሙሉ አሟልተው የተገኙ ድርጅቶች 40 ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥም ገዢው ፓርቲ ብልጽግና፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) እና ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት (አረና) እንደሚገኝበት ተሰምቷል።