ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በጌዲዎና በምእራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች በ2010 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የተገነቡ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተመረቁ።
በሀገር ወዳዱ አክቲቪስት ታማኝ በየነ አስተባባሪነት ግሎባል አሊያንስ ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው በሰበሰበው ገንዘብ እና ከዎርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር ከ37 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎ ነው ተቋማቱ የተገነቡት።
በአካባቢዎቹ ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በነበረው ግጭት በመቶ ሺኅዎች ተፈናቅለውና ለችግር ተዳርገው የነበረ ቢሆንም፤ መንግሥት በፍጥነት ወደቀዬአቸው የመመለስና ከተለያዩ አካላት ጋር የመልሶ ማቋቋም ሥራ ሢሠራ መቆየቱ ይታወሳል።
ከ37 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው እያንዳንዳቸው 3ሺኅ ሰው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዐራት የንጹህ ውኃ ግንባታዎች በጌዲዮ ዞን ጌደብ ወረዳ 855 ፣ በምእራብ ጉጂ ቀርጫ ወረዳ 855፤ በጥቅሉ በሁለቱ ዞኖች 1ሺህ 710 የመኖሪያ ቤቶችን ተገንብቶ ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ መደረጉ ታውቋል።